Search

12ኛው የጣና ፎረም በስኬት ለማካሄድ የሚያስችል አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቀቀ

ማክሰኞ ጥቅምት 03, 2019 62

"የአፍሪካ የሰላም መንገዶች፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት እና የጂኦፖለቲካዊ ሽግግር" በሚል መሪ ቃል ለሚካሄደው 12ኛው የጣና ፎረም አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ አባይ መንግስቴ ከጥቅምት 13 እስከ 15 ቀን 2017 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ ለሚካሄደው አህጉራዊ ፎረም የተደረገውን ዝግጅት አስመልክተው ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

ጉባኤው የአፍሪካውያን መሪዎች፣ ምሁራን እና ባለድርሻ አካላት በአህጉራዊ የሰላም፣ የደህንነት እና የልማት ጉዳዮች ዙሪያ በመምከር የራሳቸውን ችግሮች በራሳቸው ለመፍታት የሚያስችሉ ዘላቂ መፍትሔዎችን የሚያመላክቱበት ዋነኛ መድረክ መሆኑን ኃላፊው ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ መልካም ስም እና ገጽታዋን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የምታንጸባርቅበትን ይህን ታላቅ ፎረም በስኬት ለማጠናቀቅ ክልሉ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል።

በተለይም እንግዶች ባሕር ዳር ከተማ ከሚደርሱበት ሰዓት ጀምሮ እስከ ፎረሙ ፍጻሜ ድረስ ሂደቱ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከተማዋ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጓን ተናግረዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ በከተማዋ የሚገኙ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት ማድረጋቸውን የጠቆሙት አቶ አባይ፤ የከተማዋ ነዋሪዎች፣ አገልግሎት ሰጪዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንግዶችን በተለመደው የኢትዮጵያውያን እንግዳ ተቀባይነት እሴት በማስተናገድ የተጣለባቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የመገናኛ ብዙኃን ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሰላም፣ ልማት እና አንድነት ያላትን የማይናወጥ አቋም ከማሳየት ባሻገር፤ አፍሪካውያን ለአንድነታቸው፣ ለልማታቸው እና ለሰላማቸው አህጉራዊ ተቋማትን በመመስረት እያደረጉ ያሉትን ጥረት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በማጉላት በኩል ሚናቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

በሳሙኤል ወርቃየሁ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: