የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ አዲስ አበባ የጀመረችውን የለውጥ ጉዞ አጠናክራ በማስቀጠል ለአፍሪካ ከተሞች ተምሳሌት መሆን ጀምራለች ሲሉ ገለጹ።
ከንቲባዋ ይህንን ያሉት መዲናዋ ለሁለተኛ ጊዜ ያስተናገደችውን የ2026 የአፍሪካ ከተሞች ከንቲባዎች አመራር ኢኒሼቲቭ (AMALI) የአመራሮች ፎረም ተሳታፊዎችን በተቀበሉበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ነው።
በንግግራቸውም፣ የከተማዋ የለውጥ ጉዞ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አርቆ አሳቢነት እና ራዕይ የተቃኘ መሆኑን ጠቁመው፣ በትራንስፖርት፣ በቤቶች ልማት፣ በቴክኖሎጂ በተደገፉ አገልግሎቶች እና በትውልድ ግንባታ ላይ በሚከናወኑ ሥራዎች የነዋሪዎች ተጠቃሚነት እየተረጋገጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ከተማዋ በራሷ የፋይናንስ እና የዕውቀት አቅም ላይ ተመሥርታ በመሥራቷ ተሞክሮዋ ለሌሎች የአፍሪካ እና የዓለም ከተሞች ጠቃሚ ትምህርት እያበረከተ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
በተለይም አዲስ አበባን በአፍሪካ ሕፃናትን ለማሳደግ ምርጥ ከተማ ለማድረግ የተያዘውን ራዕይ ስኬታማ ለማድረግ፣ በሕፃናት ድገት (ECD) ላይ ያተኮሩ ተግባራት በልማት አጀንዳው ማዕከል ላይ መቀመጣቸውን አክለው ገልጸዋል።
በተጨማሪም ከAMALI መሪዎች እና የፎረሙ ተሳታፊዎች ጋር በመሆን፣ ለፕሮግራሙ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ባደረገችው ሊዛ ዲዬጎ መታሰቢያ የተሰየመውን ዘመናዊ የሕፃናት እንክብካቤ ማዕከል መርቀው ለአገልግሎት ከፍተዋል።
ከንቲባ አዳነች፣ ለመርሐ ግብሩ ስኬት አስተዋጽኦ ላደረጉት የቢግ ዊን ፊላንትሮፒ (Big Win Philanthropy) መሥራች፣ ሊቀመንበር እና ፕሬዚዳንት ጄሚ ኩፐር፣ የፋውንዴሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ከሠተ አድማሱ፣ አማካሪዎች እና የፕሮግራሙ አመራሮች በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: