Search

የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥና ሀገራዊ የስንዴ ምርታማነትን የማሳደግ ግብን ለማሳካት ሰፊ ዝግጅት ተደርጓል - ረሻድ ከማል (ዶ/ር)

ቅዳሜ ጥቅምት 07, 2019 42

በመደመር መንግሥት የተያዘውን የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥና ሀገራዊ የስንዴ ምርታማነትን የማሳደግ ግብን ለማሳካት በኦሮሚያ ክልል በደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ዞን ሰፊ ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ።

በዞኑ በዘንድሮው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከ700 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ሰብል በማልማት ከ28 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ዘመቻ መጀመሩም ተገልጿል።

ይህን ዕቅድ ለማሳካትም በተቀናጀ መልኩ ወደ ሥራ መገባቱን በኦሮሚያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ዞን አስተዳዳሪ ረሻድ ከማል (ዶ/ር)  አብራርተዋል።

በመስኖ ስንዴ ልማቱ እየተሳተፉ ያሉ የአካባቢው አርሶ አደሮች በበኩላቸው ውጤታማ ሥራ እያከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዞኑ ሊሙ ኮሳ ወረዳ የሚኖሩት አርሶ አደር ታጁ ሼኽ ኑራ እና ዜይኑ አባዱራ፣ በምርት ዘመኑ ስኬታማ የግብርና ተግባር እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እንደ ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያና የሙያ ድጋፍ ያሉ አስፈላጊ የግብርና ግብዓቶች በመንግሥት በኩል በወቅቱና በበቂ ሁኔታ በመቅረባቸው፣ በዘንድሮው የበጋ መስኖ ልማት ካለፉት ዓመታት የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።

በኦሮሚያ ክልል ደረጃ የሚካሄደው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሀገራዊ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ለኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ሲሆን፣ የደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ዞንም የዚሁ ስኬት ዋነኛ ተዋናይ በመሆን እየሠራ ይገኛል።

በራሄል አብደላ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: