ሀገራችን ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን፣ ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነትን እና ዜጋ ተኮር ዕድገትን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት በማጠናከር ወደ አዲስ የልማት ምዕራፍ እየተሸጋገረች ትገኛለች።
የቀጣይ ዓመታት የትኩረት ማዕከል ሀገራዊ አንድነትን ማጠናከር፣ አስተማማኝ ሰላምን ማስፈን፣ የኢኮኖሚ አቅምና ምርታማነትን ማሳደግ እንዲሁም ተቋማዊ አቅምን በማጎልበት የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል ላይ ያተኮረ ነው።
ሰላም ለሁሉም ልማቶች መሠረታዊ ማዕዘን በመሆኑ፣ የፖለቲካ ልዩነቶችን በሰላማዊ ውይይትና በምክክር መፍታት እንዲሁም በፌዴራል እና በክልል መካከል ያለውን ቅንጅት ማጠናከር ለሀገራዊ መረጋጋትና ለጋራ እድገት መሠረታዊ እርምጃ ተደርጎ ተይዟል።
በኢኮኖሚው ዘርፍ ከተጠቃሚነት ወደ አምራችነት በመሸጋገር የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ቁልፍ ግብ ነው። የኢንዱስትሪና የግብርና ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን ማሳደግ፣ የተፈጥሮ ሀብቶችን በአግባቡ ማልማትና የምርት ጥራትን ማሻሻል ከውጭ ጥገኝነት ለመላቀቅና ዘላቂ ዕድገትን ለማረጋገጥ የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው።
ከዚሁ ጎን ለጎን የትምህርት፣ የጤና እና የማኅበራዊ ጥበቃ አገልግሎቶች ጥራትና ተደራሽነትን ማሳደግ፣ የመንግሥት አሠራሮችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ማዘመን፣ የታክስ አስተዳደርን ማጠናከር እና በሙስና ላይ የሚደረገውን ትግል ማፋጠን ቀዳሚ ተግባራት ሆነዋል።
በተጨማሪም በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በኮሪደር ልማት፣ በግብርና እና በመሠረተ ልማት የተጀመሩ ዐበይት ሥራዎችን ማስፋፋት የሀገራችንን የልማት እምቅ አቅም እያጎለበተው ይገኛል።
የአካባቢ ጥበቃን ማሳደግ፣ የከተሞችን ገጽታ እና አገልግሎት ማሻሻል፣ የገጠርና የከተማ ልማትን ማስተሳሰር እና የመሠረተ ልማት አቅምን ማሳደግ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን በከፍተኛ ደረጃ እያፋጠኑት ይገኛሉ።
እነዚህን የልማት ራዕዮች ወደ ተጨባጭ ውጤት ለመቀየር የፕሮጀክቶችን አፈጻጸም የማፋጠን፣ ተጠያቂነትንና ግልጽነትን የማረጋገጥ፣ የዜጎችን ንቁ ተሳትፎ የማሳደግ እንዲሁም የመከላከያ እና የጸጥታ ተቋማትን ዘመናዊ አቅም የማጠናከር ሥራዎች በተግባር እየተከናወኑ ይገኛሉ።
የእነዚህ የትኩረት አቅጣጫዎች ስኬት በቁርጠኝነት፣ በተቋማት ቅንጅትና በሕዝብ ትብብር ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ በጋራ በመሥራት የሀገራችንን የብልጽግና ራዕይ ወደ ሙሉ ተግባር መለወጥ ይቻላል።
በኢንቲሃድ አብራር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: