በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሰማይ ሥር ከተዘሩት እጅግ አደገኛ የትርክት ስህተቶች መካከል፣ የአንድን ታላቅ ሕዝብ ዘላቂ ሕልውና ከአንድ የፖለቲካ ድርጅት ዕድሜ ጋር አስተሳስሮ መመልከት ግንባር ቀደሙ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኢቢሲ ጋር በትግርኛ ቋንቋ ባደረጉት ቆይታ፣ ይህንን የተዛባ እሳቤ ከሥሩ ነቅለውታል። የትግራይ ሕዝብ ለሺህ ዓመታት የኖረ እና ወደፊትም በክብር የሚኖር የታሪክ ባለቤት እንጂ፣ የ50 ዓመት ዕድሜ ካለው እና እየከሰመ ካለው ህወሓት ጋር የተቆራኘ አይደለም።
እንደ አጼ ዮሐንስ ያሉ ነገሥታት አልፈው ሕዝቡ ግን ጸንቶ እንደቀጠለ ሁሉ፣ መሪዎች እና ድርጅቶች እንደ ወቅት ደመና ይመጣሉ፣ ይሄዳሉ፤ ሕዝብ እና ሀገር ግን ዘላለማዊ ናቸው ብለዋል።
ህወሓት በትግራይ አፈር ላይ ቢበቅልም፣ በትጥቅ ትግሉ ማግስት የትግራይን ወጣት በፈንጂ ከማስጨረስ እና አርሶ አደሩን ‘መሳፍንት’ የሚል ስም እየሰጠ በጉድጓድ ከመቅበር አንሥቶ፣ የትግል አጋሮቹን እራት ጋብዞ በተኙበት እስከ መፍጀት የደረሰው ታሪኩ፣ ድርጅቱ ቅንጣት ታክል የትግራዋይነት ጨዋነት እና ሰብዓዊ ርኅራኄ እንዳልነበረው ሕያው ምስክር ነው።
ይህ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” የሚል የድርጅቱ ባሕርይ፣ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የተገኘውን ወርቃማ ዕድል እንዲጨናገፍ አድርጎታል። የፌዴራል መንግሥቱ ለሰላም ሲል መሠረታዊ አገልግሎቶችን ቢመልስም፣ ቡድኑ ግን ትጥቅ ከመፍታት ይልቅ ዳግም ወደ መሣሪያ ልመና እና ወጣቶችን በግዳጅ ወደ ማፈስ ተመልሷል።
ተፈናቃዮችን ለፖለቲካ ቁማር በመያዣነት በመጠቀም፣ የዕርዳታ እህልን ነጥቆ ለጥይት መግዣ በማዋል እንዲሁም የባንክ፣ የቴሌኮም እና የአየር ትራንስፖርትን በማስተጓጎል በድርቅ የተጎዳውን ሕዝብ ለከፋ መከራ አጋልጦታል።
መላው ኢትዮጵያ የኮሪደር እና ሌሎች ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ ባለበት በዚህ ወቅት፣ በትግራይ ግን ባለፉት ስድስት ዓመታት አንዲት ጋት የልማት ሥራ አለመከናወኑ አሳዛኝ ሐቅ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ።
የድርጅቱ መሪዎች ልጆቻቸውን በውጭ ሀገራት እና በአዲስ አበባ አስቀምጠው በወርቅ ንግድ እና በፎቅ ግንባታ ሲምነሸነሹ፣ የድሃው ልጅ ግን በመቐለ ጎዳናዎች አካሉ ጎድሎ በድህነት መማቀቁ የአገዛዙን ግብዝነት እርቃኑን ያስቀረዋል።
የድርጅቱ የፖለቲካ ክስረት የተረጋገጠው ደግሞ በፈጠረው መርሕ አልባ እና ‘ግልብጥብጥ’ ጥምረት ውስጥ ነው። ትናንት “ታግዬ አመጣሁት” የሚለውን ሕገ መንግሥት ከማይቀበሉ የሀገር ውስጥ ሽፍቶች፣ እንዲሁም የአጼ ዮሐንስን እና የራስ አሉላን ታሪክ በየዕለቱ ከሚያጠለሹ የውጭ ኃይሎች ጋር መሻረኩ የሞራል ልሽቀቱን ያሳያል።
በተለይም በአንድ ወቅት ከ300 በላይ ፋብሪካዎች የነበሯትን ኤርትራን ወደ ፍርስራሽነት ከቀየረው እና ውቢቷን አስመራን አናሳ ሆና እንድትገኝ ካደረገው ሻዕቢያ (ሕግደፍ) ጋር መተባበሩ የጥፋት ጥጉ ነው።
ልማትን ትቶ የኢትዮጵያ ጠላቶች መሣሪያ መሆንን የመረጠው የኤርትራ መንግሥት፣ የውጭ ‘አይዞህ ባዮች’ ጥይት ከማቀበል ባለፈ የራሳቸውንም ችግር መፍታት እንደማይችሉ ተረድቶ ወደ መልካም ጉርብት እና ካልተመለሰ፣ የሚከተለው መዘዝ እጅግ መራራ እንደሚሆን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማስጠንቀቂያ ግልጽ መልዕክት አስተላልፏል።
ዛሬ የትግራይ ሕዝብ በታሪካዊ መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆሟል። ሕዝቡ ክልሉን ራያ፣ አሽዓ፣ አጋሜ እና እንደርታ እያለ በጎጥ ከፋፍሎ እንደ ግል ኩባንያ ይዘውር የነበረውን የአንድ ቡድን አገዛዝ አሽቀንጥሮ በመጣል፣ ወደ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እና መልሶ ግንባታ የሚሸጋገርበት ሰዓት አሁን ነው።
በዚህም የትግራይ ወጣት እጁን ከቃታ አንሥቶ ወደ ኮምፒውተር፣ ወደ ዩኒቨርሲቲ እና ፋብሪካ ሊመለስ፣ የፖለቲካ ልሂቃኑም ከስደት ውርደት ይልቅ በሀገራቸው ሕግ እና ሰላም ጥላ ሥር ሊሰባሰቡ ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥሪ አቅርበዋል።
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: