Search

የውጪ ጣልቃ ገብነትን የሻረው የኢትዮጵያ አዲሱ የፖለቲካ ባህል

ረቡዕ ጥቅምት 11, 2019 53

የሀገርን ዘላቂ ሰላም፣ ሉዓላዊነት እና የፖለቲካ ነጻነት ማረጋገጥ የሚጀምረው ከዜጎች ልብ እና አዕምሮ ነው።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት  በታሪኳ አዲስ እና ወሳኝ የለውጥ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች፤ ይኸውም የውጪ ኃይሎችን አጀንዳ እና የጥቅም ግፊት ከመሸከም ወጥታ፣ በራሷ ዜጎች የጋራ ውይይት እና ፍላጎት የተቃኘ፣ ከተላላኪነት የፀዳ የፖለቲካ ባህልን ለማስረጽ የጀመረችው ጉዞ ነው።

ከውጪ ተላላኪነት የፀዳ የፖለቲካ ባህልን ማስፈን ማለት፣ የባዕዳን ፍላጎት አስፈጻሚ ከመሆን ሙሉ በሙሉ ተላቅቆ የኢትዮጵያ ሕዝብን ሁለንተናዊ ጥቅም፣ ወንድማማችነት እና ሀገራዊ አንድነት የሚያስቀድም ሥርዓት መገንባት ማለት ነው።

እናም ለዘመናት በውጪ ርዕዮተ-ዓለሞች እና ጣልቃ ገብነቶች እንዲሁም በውስጥ ልዩነቶች እና ሽኩቻዎች ሲናጥ የነበረው የፖለቲካ ምህዳራችን፣ አሁን ላይ በሀገር በቀል አስተዳደራዊ ጥበቦች እና እሴቶች እየተቃኘ ይገኛል።

በዚህ ታሪካዊ የሽግግር ወቅት ደግሞ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሂደት እና ወደ ትግበራ የገባው ውጤቱ ትልቅ የለውጥ ማዕበል ይዞ መጥቷል።

የሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ኢትዮጵያውያን በታሪካችን፣ በፖለቲካዊ ልዩነቶቻችን እና በሀገራዊ አቅጣጫዎቻችን ላይ ያለ ውጪ ጣልቃ ገብነት እና ተጽዕኖ በነጻነት ተቀምጠን የመከርንበት፣ ቅሬታዎቻችንን የፈተንበት ብሔራዊ እና የጋራ መግባባት የፈጠርንበት ታላቅ ሀገራዊ መድረክ ነው።

ምክክሩ በውጪ ኃይሎች ረቂቅ እና መመሪያ ሳይሆን፣ በራሳችን ባህልና እሴት ላይ ተመስርቶ የተካሄደ በመሆኑ፣ የፖለቲካ ባህላችንን ከጥል እና ከሴራ ወደ ሰላማዊ ውይይት የሚያሸጋግር ነው።

ይህም የኢትዮጵያ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን ብቃት ያለው መሆኑን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተጨባጭ ያሳየንበት የዴሞክራሲያዊ ሉዓላዊነታችን መገለጫ ነው።

የዚህ የብሔራዊ መግባባት አዲስ የፖለቲካ ባህል ዋና ባለቤት ራሱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው።

የውጪ አጀንዳን እንደ እውነት አድርጎ ከመቀበል ይልቅ፣ ሀገራዊ ጥቅምን አስቀድሞ ማሰብ እና በውይይት ሂደት ተሳታፊ መሆን የነቃ ትውልድ መለያ ነው።

ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ በፅናት የምትገነባው የፖለቲካ ነጻነት ለነገዋ ኃያል፣ ሰላማዊ እና የተረጋጋች ሀገር መሠረት የሚጥል ታሪካዊ እርምጃ ነው።

በሔዋን ጌታቸው

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: