የመደመር መንግሥት የሀገርን ጥቅም በማስከበር እና ትልቅ ራዕይ ያላትን ታላቅ ሀገር ዕውን ለማድረግ በቁርጠኝነት እየሠራ እንደሚገኝ የኦሮሚያ ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ገለጹ።
አቶ ኃይሉ አዱኛ በሰጡት መግለጫ የጠላት ኃይሎች ሀገራችን እያስመዘገበች ያለችውን ዕድገት በማደናቀፍ የሀገርን ሰላም እና መረጋጋት ለማደፍረስ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ መቼም ቢሆን እንደማይሳካ ገልጸዋል።
ራሱን 'ፅምዶ' ብሎ የሚጠራው ኃይል እየደረሰበት ባለው ኪሳራ የተነሣ የመንግሥትን ትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየር እና የውስጥ ግጭትን ለማስፋፋት እየተፍጨረጨረ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በዚሁ መሠረት ሀገር በማፍረስ ሥራ ላይ የተሰማራው 'ፅምዶ' የተባለው አሸባሪ ቡድን በደቡብ ምሥራቅ ኦሮሚያ፣ አርሲ ዞን ሲርካ ወረዳ ጮሌ እና ቢርቦ ቀበሌዎች ውስጥ በንጹሐን ዜጎች ላይ ላደረሰው የሕይወት እና የንብረት ጉዳት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የተሰማውን ኀዘን ገልጿል።
ክልሉ ይህንን ጥፋት በፈጸሙ አካላት ላይ የጀመረውን እርምጃ ከሕዝቡ ጋር በመሆን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ኃይሉ አስታውቀዋል።
በተጨማሪም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በዚህ ችግር ምክንያት ለተጎዱ እና ከቀዬአቸው እና ከንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ከሕዝቡ ጋር በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አቶ ኃይሉ ጠቁመዋል።
በሐምራዊት ብርሃኑ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: