Search

የሰላም አየር በትግራይ

እሑድ ጥቅምት 29, 2019 117

ሕገ-ወጡ የህወሓት ቡድን የፕሪቶሪያውን ታሪካዊ የሰላም ስምምነት ተከትሎ የተገኘውን የሰላም ጭላንጭል ለማጨለም የመረጠው የጥፋት መንገድ ክልሉን ዳግም ወደ አለመረጋጋት እና ወደ ከፋ የሕልውና ቀውስ ውስጥ ከትቶት ቆይቷል።

የትግራይ ሕዝብ ባለፉት ዓመታት የዚህ ጽንፈኛ ቡድን እኩይ ፍላጎት ሰለባ በመሆን የወጣቶች ሕይወት መጥፋት፣ የንብረት ውድመት፣ የኢኮኖሚ ድቀት እና የማይተካ ማኅበራዊ ቀውስ ደርሶበታል።

በሌሎች አካባቢዎች የተስፋፋው የልማት ዕድል ለትግራይ እንዳይደርስ፣ የትግራይ ሕፃናት እና ወጣቶች ከትምህርት ገበታቸው እንዲፈናቀሉ፣ የትግራይ እናቶች የወላድ መካን እንዲሆኑ እና ክልሉ ከነባራዊ የዓለም ሁኔታ እንዲገለል ምክንያት ሆኗል፡፡

እንደዚህ ዓይነቱን እኩይ ተግባር “በቃኝ!” ያለው የትግራይ ሕዝብ የቡድኑ ሕልውና እንዲከስም በማድረግ ለሰላም ያለውን ጽኑ ፍላጎት በገሃድ አሳይቷል። 

የፌዴራል መንግሥትም ሕገ-መንግሥታዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 62(9) መሠረት ጊዜያዊ የፌዴራል ባለአደራ አስተዳደር በማቋቋም በክልሉ የሕግ የበላይነትን፣ ሰላምን እና ፀጥታን ማረጋገጥ ችሏል።

ይህ ወሳኝ እርምጃ የሕዝቡን ደኅንነት ከመጠበቁም በላይ ለአካባቢው አዲስ የተስፋ ብርሃን ፈንጥቋል።

በግጭቱ ምክንያት ተቋርጠው የነበሩ መሠረታዊ አገልግሎቶች በፍጥነት እንዲመለሱ ተደርጓል።

የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የቴሌኮሙኒኬሽን፣ የባንክ አገልግሎቶች እና የንግድ አየር የበረራ መስመሮች እንደገና ሥራ በመጀመራቸው የማኅበረሰቡ ዕለታዊ ሕይወት እና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ወደ ነበረበት እየተመለሰ ይገኛል።

ከዚህም በላይ ሰብአዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ወገኖች በአስቸኳይ ለመደገፍ ሰፊ የዕርዳታ አቅርቦት ስርጭት ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በመቀናጀት ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን በኩል የጦር መሣሪያዎችን የመፍታት፣ ታጣቂዎችን ወደ ማኅበረሰቡ የመመለስ እና የማቋቋም ሥራ (DDR) በስፋት እየተከናወነ ይገኛል።

ዛሬ የትግራይ ሕዝብ ለረጅም ጊዜ ተጭኖበት ከነበረው የአምባገነንነት፣ የሰቀቀን እና የስጋት ድባብ ሙሉ በሙሉ ወጥቶ ታላቅ እፎይታ አግኝቷል።

አሁን በክልሉ እየነፈሰ ያለው የሰላም እና የዕርቅ አየር የሕዝቡን ልብ በታላቅ ተስፋ ሞልቶታል።

በየአካባቢው የሚታየው የተረጋጋ መንፈስ፣ የልማት መነቃቃት እና የጋራ የሕይወት ትንሣኤ ሕዝቡ የሰላምን ጣዕም በቅጡ እንዲቀምሰው አድርጎታል።

ሕዝቡ አዲሱ ባለአደራ አስተዳደር ያቀረበውን የሰላም፣ የልማት እና የወደፊት ተስፋ ጥሪ በደስታ በመቀበል ከአስተዳደሩ ጎን በጽናት በመቆም የሰላም እና ፀጥታ ማስከበር፣ የኮሪደር ልማት እና የአካባቢ ግጭቶችን የመከላከል ሥራዎች ላይ ንቁ ትብብር እያደረገ ይገኛል።

ማኅበረሰቡ ሰላሙን ለማጽናት በየአካባቢው አድፍጠው የሕዝብን ሰላም ለመንሣት ያሰፈሰፉ የሕገ-ወጡ ቡድን ርዥራዦችን በማጋለጥ እና አሳልፎ በመስጠት ላይ ይገኛል።

ይህ የተቀናጀ እና ሕዝባዊ ጥረት ክልሉን ወደ ዘላቂ ሰላም፣ ዴሞክራሲ እና ብልጽግና አዲስ ምዕራፍ በይፋ እያሸጋገረው ይገኛል።

በለሚ ታደሰ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: