Search

የመደመር መንግሥት መጽሐፍ ዜጎች ከመሰረታዊ ፍላጎት ባሻገር በክብር የመኖር ህልማቸውን ለመመለስ አቅጣጫ ያስቀመጠ ነው - አቶ ጌታቸው ረዳ

ረቡዕ መስከረም 07, 2018 41

የመደመር መንግሥት መጽሐፍ ዜጎች ከመሰረታዊ ፍላጎት ባሻገር በክብር የመኖር ህልማቸውን ለመመለስ አቅጣጫ ያስቀመጠ ነው ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ ገለጹ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጻፈው የመደመር መንግሥት መጽሃፍ ዛሬ ለንባብ በቅቷል።
በመጽሐፉ የምረቃ መርሐ-ግብር ላይ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ፣ የመጽሃፉ ደራሲና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች፣ እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ታድመዋል።
በመጽሐፍ ላይ ዳሰሳ ካቀረቡት መካከል የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ እንዳሉት፣ መጽሃፉ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ሁኔታ የሚያስቃኝ ነው።
በተለይ የኢትዮጵያ ችግሮችን በጥልቅ የዳሰሰ እና ተግባራዊ መፍትሄዎችን ያመላከተ መሆኑንም ተናግረዋል።
መጽሐፉ አስተሳሰብ ላይ ትኩረት አድርጎ ከቁጭት እንደሚነሳ ጠቅሰው፣ ይህም ችግሮችን ከመሰረቱ ለመፍታት ወሳኝ መሆኑን ነው ያብራሩት።
መጽሐፉ ነገሮችን አፍርሶ ከመስራት ይልቅ አዎንታዊውን ማስቀጠል፣ አሉታዊውን ደግሞ ማስተካከልን እንደሚያመላክትም አንስተዋል።
ይህም ኢትዮጵያ ለዘመናት የሄደችበትን ተቸካይ የፖለቲካ አካሄድ የቀየረ አተያይ ስለመሆኑም አብራርተዋል።
መጽሃፉ ፖለቲካችንን ያሸነፈ አካል እንደፈለገ ሁሉን ይጠቅልል ከሚል አካሄድ የሚያወጣ ነው ብለዋል።
''እኔ የፈለኩት ካልሆነ'' ከሚል የዜሮ ድምር ጨዋታ መውጣት የሚቻልበትን ዘመናዊ የፖለቲካ አካሄድ ያመላከተ ስለመሆኑም አቶ ጌታቸው አብራርተዋል።
በሌላ በኩል ዜጎች ከመሰረታዊ ፍላጎት ባሻገር በክብር የመኖር ህልማቸውን ለመመለስ አቅጣጫ ያስቀመጠ መሆኑንም እንዲሁ።
የኢትዮጵያ ችግሮች በነበረው አካሄድ ትርጉም ባለው መልኩ መፍታት እንደማይቻል አንስተው፣ የመደመር እሳቤ ተግባራዊ ያደረገው መፍጠርና መፍጠን በዚህ ረገድ ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማን የተከማቸ ችግር ለመፍታት የተተገበረው የመፍጠርና መፍጠን መፍትሄ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ መሆኑንም ተናግረዋል።
አዲስ አበባን ለመለወጥ የተጀመረው ሥራ አዲስ የሥራ ባህልን ያለማመደ መሆኑንም ገልጸዋል።
በቀጣይ በአዲስ አበባ የታየው አዲስ ተስፋ ወደ ሁሉም የኢትዮጵያ አቅጣጫ እንዲሰፋ መረባረብ ይገባል ነው ያሉት።
መጽሃፉ ለማንበብ ምቹ በሆነ አቀራረብ መዘጋጀቱን የተናገሩት አቶ ጌታቸው፣ ሁሉም እንዲያነበውም ጥሪ አቅርበዋል።
#ebcdotstream #​የመደመርመንግሥት #AbiyAhmedAli

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ተያያዥ ዜናዎች: