አውሮፓን እያናወጠ የሚገኘው አስከፊ የሙቀት ማዕበል በሰው ልጅ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ምክንያት በመጣው የአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የተከሰተ መሆኑን ሳይንቲስቶች በጥናት አረጋገጡ።
አርብ ዕለት ይፋ በሆነው የዓለም የአየር ንብረት የሳይንቲስቶች ቡድን አዲስ ሪፖርት መሠረት፣ አብዛኛውን የአውሮፓ ክፍል እያዳረሰ ያለው ከፍተኛ የሙቀት መጠን በቀጣናው እስካሁን ከተመዘገቡት የሙቀት ማዕበሎች ሁሉ “እጅግ ከባድ” ያደርገዋል።
በዚህ ሳምንት በፈረንሳይ፣ ጣሊያን፣ ስፔን፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና በሌሎችም የአውሮፓ ሀገራት የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ከፍተኛ ሙቀት እያጋጠማቸው ሲሆን፣ በብዙ ቦታዎች የቀኑ የሙቀት መጠን ከ40 ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ ሆኖ በተጨባጭ ተመዝግቧል።
ይህ አስከፊ የሙቀት ማዕበል አሁን ላይ ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ እየተጓዘ መሆኑ የተዘገበ ሲሆን፤ በአህጉሪቱ ምዕራባዊ ክፍሎች በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለሕልፈት የዳረገው፣ የሕክምና አገልግሎቶችን ያጨናነቀውና ኢኮኖሚውን ያዛባው ይህ አስከፊ ሁኔታ በዚህ ከቀጠለ በጀርመን እና በመካከለኛው አውሮፓ ላይ ሊደገም ይችላል የሚል ትልቅ ሥጋትን ፈጥሯል።
የዓለም የአየር ትንበያ ግምትን እንዲሁም የሳይንቲስቶችን ጥናት ዋቢ አድርጎ አልጀዚራ በሰፊው እንደዘገበው፣ አውሮፓ በተመሳሳይ ሁኔታ ረዘም ላለ ጊዜ በከፍተኛ ሙቀት ተመትታ የነበረችው እ.አ.አ በሰኔ 1976 ዓ.ም ነበር።
ጥናቱ በጥልቀት እንደሚያመለክተው ከሆነ፣ በአህጉሪቱ ሌላኛው አስከፊ የተባለው የ2003ቱ ታሪካዊ ክስተት ወቅትም ቢሆን የሙቀት መጠኑ አሁን ካለው በ2 ዲግሪ ሴልሺየስ ያህል ቀዝቃዛ ነበር።
ይህ ትንተና እንደሚያሳየው ከፍተኛ ሙቀት በሰዎች የሕይወት ዘመን ትውስታ ውስጥ እንኳ ሳይቀር በፍጥነት እየጨመረ የመጣ ሲሆን፣ እንዲህ ያሉ አደገኛ ክስተቶች ከ2003 ወዲህ ከደርዘን እስከ መቶ እጥፍ የበለጠ የመከሰት ዕድላቸው የሰፋ ሲሆን፣ ከ50 ዓመታት በፊት ግን ጨርሶ የማይታሰቡ ነበሩ።
የለንደኑ ኢምፔሪያል ኮሌጅ ባልደረባና የጥናቱ ዋና አዘጋጅ ቲዎዶር ኪፒንግ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ የሙቀት ማዕበሉ በዚህ ደረጃ በሰኔ ወር ሊከሰት የቻለው በቀጥታ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት መሆኑን አረጋግጠዋል።
በፈረንሳይ ፓሪስ በተከሰተው ከባድ የሙቀት ማዕበል እና በሕክምና ተቋማት ላይ በደረሰው ከፍተኛ ጫና ምክንያት፣ በከተማዋ ሊካሄዱ የነበሩ የተለያዩ ፕሮግራሞች ወደ ሌላ ጊዜ መተላለፋቸውን ሮይተርስ በዘገባው አመልክቷል።
ይህ ክስተት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚመጡ የተፈጥሮ ቀውሶች በሰዎች የዕለት ተዕለት ሕይወት፣ በሕክምና ተቋማትና በታላላቅ ዓለም አቀፍ ሁነቶች ላይ እያሳደሩ ያሉትን ከባድና አስከፊ ተፅዕኖ በተግባር ያሳየ መሆኑ ተመላክቷል።
በመሐመድ ፊጣሞ