Search

የቢሊዮን ዶላሮች ስኬት፤ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ያመጣቸው ትልልቅ ለውጦች

ዓርብ ሰኔ 19, 2018 56

ባለፉት አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ የተካሄዱት ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የሀገራችንን የነገ ዕጣ ፈንታ የቀየሩ ታሪካዊ መዋቅራዊ ሽግግሮች ናቸው።

ቀደም ሲል በጽኑ የፋይናንስ መሠረት ላይ ያልተገነባውና ማክሮ ኢኮኖሚያዊ መዛባቶች የወለደው የትናንቱ ሥርዓት፣ ዛሬ ቦታውን "ሀገር በቀል በሆነ የኢኮኖሚ ማሻሻያ" መርሃ ግብር እየተካ ነው። ይህ የፖሊሲ አቅጣጫ በአቅርቦትና ፍላጎት፣ በመንግሥት ገቢና ወጪ እንዲሁም በወጪ ንግድ ሚዛን መካከል የነበሩ የሰፉ ክፍተቶችን በመድፈን ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን እያስመዘገበ ይገኛል።

የማሻሻያው ትልቁ ፍልስፍናዊ ትርጉምም የሀገራችንን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት በተግባር ማረጋገጥና የዘርፎችን ምርታማነት በማሳደግ የዜጎችን ቀጥተኛ ተጠቃሚነት ዕውን ማድረግ ላይ ያተኮረ ነው።

የዚህ ሽግግር ትልቁ ማሳያና የኢኮኖሚው ጀርባ አጥንት የሆነው የግብርናው ዘርፍ ከባሕላዊና ለዕለት ፍጆታ ብቻ ከሚውልበት የዘመናት አዙሪት ወጥቶ ወደ ዘመናዊና ቴክኖሎጂ ተኮር ሥርዓት መሻገሩ ነው።

በተለይም በበጋ የስንዴ ልማት የተመዘገበው ስኬት ኢትዮጵያ ለስንዴ ግዢ በዓመት ታወጣ የነበረውን ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማዳን ብቻ ሳይሆን፣ ምርቱን ወደ ውጭ መላክ እንድትጀምር አድርጓታል።

ይህ ስኬት ኢትዮጵያ ለዘመናት ከተሸከመችው የምግብ ተመጽዋችነት ቀንበር ወጥታ የምግብ ሉዓላዊነቷን በራሷ ክንድ እንድታረጋግጥ የሞራልና የስነልቦና ስንቅ ሆኗታል።

በሌላ በኩል የወደፊቱን ዓለም ለመቀላቀል የተዘረጋው የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ሁለንተናዊ ገጽታን እያደሰ ነው። "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025" እና "2030" የተሰኙት ግዙፍ ዕቅዶች ኢትዮጵያን የአፍሪካ የቴክኖሎጂ ማዕከል የማድረግ ራዕይ ሰንቀዋል።

በዚህ ውስጥ የ"5 ሚሊዮን ኮደሮች" ኢኒሼቲቭ ወጣቶች የዲጂታል ክህሎት ኖሯቸው የሥራ ዕድልና ሀብት እንዲፈጥሩ በማድረግ ረገድ የፈጠረው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አንቀሳቃሽ ኃይል በቀላሉ የሚገመት አይደለም።

ከዚሁ ጎን ለጎን፣ የፋይናንስ ሥርዓቱን በማዘመን የውጭ ምንዛሬ ክምችትን ለማሳደግ የተወሰዱት እርምጃዎች ውጤት እያሳዩ ሲሆን፣ ባለፉት አምስት ዓመታት 18.6 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መሳብ መቻሉ የፖሊሲዎቹን አስተማማኝነት በተግባር ያሳያል።

የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍም በ"ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ አማካኝነት አዲስ የሕይወት እስትንፋስ አግኝቷል። የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ወደ 67 በመቶ ማድረስ መቻሉና ቀደም ሲል ተዘግተው የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፋብሪካዎች ወደ ሥራ መመለሳቸው የሀገር ውስጥ ምርትን በማሳደግ የገቢ ምርቶችን ለመተካት አስችሏል። ይህም በበጀት ዓመቱ የኢንዱስትሪ ዘርፉን በ12.8 በመቶ ለማሳደግ ለተቀመጠው ግብ ትልቅ መነሻ ሆኗል።

በተጨማሪም የሐዋላ (ሬሚታንስ) ፍሰት እንዲጨምር በተደረገው ጥረት በ2017 መጨረሻ ገቢው ወደ 7.06 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ማለቱና መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ የሚወስደው ቀጥታ ብድር እንዲቀር መደረጉ የዋጋ ንረትን በመግታት ረገድ የጎላ ፋይዳ አበርክቷል። የፋይናንስ ሥርዓቱን ግልፅነትና ተወዳዳሪነት በማስፈን ለግል ባለሀብቶችና ለውጭ ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የታየው ቁርጠኝነት የኢኮኖሚውን መዋቅር ከውስጥ ወደ ውጭ ለውጦታል።

እነዚህ ባለፉት አምስት ዓመታት የተመዘገቡ ስኬቶች የቅንጦት ውጤቶች ሳይሆኑ ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ተወዳዳሪ፣ የብልጽግናዋ ማማ ላይ የወጣችና በራሷ የምትተማመን ሀገር ለማድረግ ለተጀመረው ታላቅ የትውልድ ጉዞ የማይናወጥ መሠረት የጣሉ ድሎች ናቸው።

በበረከት ሽመልስ