የባሕር በር ባለቤት መሆን ከኢኮኖሚያዊ ፍላጎት ባሻገር፣ የሕዝብን አመለካከትና የሀገርን ዕጣ ፈንታ ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሻግር የሥልጣኔ ቁልፍ መሆኑ ይታወቃል።
የወደብ አልባነት ሥነ-ልቦና ሀገርን በህልውና አጥር ውስጥ የሚያስር ሲሆን፤ የባሕር በር ባለቤትነት ግን በየብስ መታጠርን ግንብ ሰብሮ ሀገርን በንግድ፣ በባህልና በአዳዲስ እሳቤዎች ወደምትታደስ ምድር የሚቀይር ወሰን-አልባ የመንቀሳቀስ ነጻነትን ያጎናጽፋል።
የባሕር በር አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ከመሆኑም በላይ፣ ሀገርን በዘመናዊው "ሰማያዊ ኢኮኖሚ" ውድድር ውስጥ እንድትሳተፍ እድል የሚሰጥ ነው።
በዚህም የመርከብ ግንባታን፣ ሎጂስቲክስን፣ የዓሳ ሀብትን፣ ቱሪዝምንና የባሕር ላይ ኢነርጂን በከፍተኛ ሁኔታ በመቀስቀስ፣ ወደቦች ለልዩ ኢኮኖሚ ቀጣናዎችና ለቴክኖሎጂ ኮሪደሮች ዋነኛ መግቢያ በር እንዲሆኑ ያስችላል።
ይህ ዓይነቱ ወሰን-አልባ ሽግግር ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት መሠረት ከመሆኑም በላይ፣ ደረቅ ምድርን ብቻ የሚያውቁ እና የሚያስቡ ተማሪዎች እና ወጣቶች የባሕር ባዮሎጂስት፣ የመርከብ ካፒቴን ወይም የውቅያኖስ ቴክኖሎጂ ፈጣሪ የመሆን አዳዲስ ታላላቅ ሕልሞችን እንዲያልሙ ሰፊ ምናባዊ ነጻነትን ያጎናጽፋል።
ሀገራችን ኢትዮጵያም ቀደም ሲል በሴራ ያጣችውን የባሕር በር ዳግም ለማግኘት ታሪካዊ እና ሕጋዊ መብቶችን አጣቅሳ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጉዳዩን በአግባቡ እንዲገነዘበውና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ምላሽ እንዲሰጥበት በቁርጠኝነት እየሠራች ትገኛለች።
ታሪካዊና ሕጋዊ መብቶቻችንን ለማስከበር በሚደረገው በዚህ ሁለንተናዊ ጥረት ውስጥ መላው ትውልድ በዕውቀትና በንቃት በመሳተፍ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል።
በመሐመድ ፊጣሞ