አፕል ኩባንያ በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ ሁኔታዎች በቅርበት ለመመልከትና አብሮ ለመሥራት ፍላጎት እንዳለው የኩባንያው ተወካዮች ገለፁ፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነሮች አቶ ዳጋቶ ኩምቤ እና አቶ ዝናቡ ይርጋ ከአፕል የሕዝብ ፖሊሲ እና የመንግሥት ጉዳዮች በአፍሪካ ኃላፊ አልፋ ባሪ እና ከኩባንያው የታዳጊ ገበያዎች የሕዝብ ፖሊሲ ዓለም አቀፍ ኃላፊ ዓሊ ኻናፈን ጋር ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱ ወቅት ምክትል ኮሚሽነሮቹ የኢትዮጵያን ተስፋ ሰጪ የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ እንዲሁም መንግሥት ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ የሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት ገልጸዋል።
በተለይም እንደ አፕል ያሉ ተጽዕኖ ፈጣሪ ተቋማት በሀገሪቱ ያለውን ሰፊ ገበያና የሰለጠነ ወጣት የሰው ኃይል በመጠቀም ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በዲጂታል 2030 ስትራቴጂ፣ በአይሲቲ ፓርክ ግንባታ፣ በቴሌኮም እና የንግድ ዘርፉን ለውጭ ውድድር ክፍት በማድረግ በአፍሪካ ተመራጭ የቴክኖሎጂ ኢንቨስትመንት ማዕከል ለመሆን እየሠራች እንደምትገኝ ምክትል ኮሚሽነሮቹ አብራርተዋል።
የአፕል ተወካይ ዓሊ ኻናፈን በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው ዘርፍ እያሳየች ያለውን ፈጣን ዕድገትና የፖሊሲ ማሻሻያ አድንቀዋል፡፡
ኩባንያቸው በታዳጊ ገበያዎች ላይ ያለውን ተደራሽነት ለማስፋት በሚያደርገው እንቅስቃሴ ውስጥ የኢትዮጵያን ምቹ ሁኔታዎች በቅርበት ለመመልከትና አብሮ ለመሥራት ፍላጎት እንዳለው መግለጻቸውን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃ አመልክቷል።