ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች ስለ ሀገራችን የቱሪስት መዳረሻዎች በቂ መረጃ የሚያገኙበት ዘመናዊ የቨርቹዋል ማዕከል በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መንገደኞች መውጫ ስፍራ ላይ ሊገነባ መሆኑ ተገለፀ።
ይህንን ዘመናዊ አገራዊ የመረጃ ማዕከል በጋራ ለመገንባት የሚያስችለውን ስምምነት የቱሪዝም ሚኒስቴር ከቶፓን ኢትዮጵያ (Topan Ethiopia) ከተባለ ተቋም ጋር በይፋ ተፈራርሟል።
በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴዔታ አቶ ስለሺ ግርማ እና የቶፓን ኢትዮጵያ ተወካይ ቃልኪዳን አረጋ የጋራ መግባቢያ ሰነዱን ተለዋውጠዋል።
በተደረሰው ስምምነት መሠረት ለዲጂታል ማዕከሉ ግንባታ የሚያስፈልገውን አጠቃላይ ወጪ ሁለቱ ተቋማት በጋራ የሚሸፍኑት ሲሆን፣ የቴክኖሎጂ ማዕከሉን የመገንባትና እውን የማድረግ ኃላፊነት ደግሞ ለቶፓን ኢትዮጵያ ተሰጥቷል።
ይህ በዓይነቱ ልዩ የሆነ የቨርቹዋል መረጃ ማዕከል በቀጣይ አሁን እየተገነባ በሚገኘው አዲሱ ትልቅ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥም ተካቶ አገልግሎት እንዲሰጥ እንደሚደረግ ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።