ኤፍራጥስ እና ጤግሮስ ከቱርኪዬ ምድር ተነሥተው ወደ ሶሪያ እና ኢራቅ የሚፈስሱ ጥንታዊ ወንዞች ናቸው።
ቱርኪዬ ታዲያ በእነዚህ ወንዞች ላይ 22 የመስኖ እና 19 የኃይል ማመንጫ ግድቦችን ለመሥራት አቅዳ፣ እስከአሁንም 13 የመስኖ እና 14 የኃይል ማመንጫ ግድቦችን አጠናቅቃ እየተጠቀመችባቸው እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።
የቱርኪዬ የድንበር ተሻጋሪ የውኃ አስተዳደር ስትራቴጂ በዋነኛነት በተፋሰሱ ሀገራት መካከል የትብብር መርሆዎችን የተከተለ ሲሆን፣ የማንኛውንም ሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት አይቀበልም።
"የውኃ ዲፕሎማሲ" ተብሎ የሚጠራው የቱርኪዬ የውኃ አስተዳደር ፖሊሲ፣ ለተፋሰሱ ሀገራት ትብብር እና የጋራ የውኃ አስተዳደር ቅድሚያ ይሰጣል።

እያንዳንዱ የተፋሰስ ሀገር በግዛቱ ውስጥ ያለውን የውኃ ሀብት የመጠቀም ሉዓላዊ መብት እንዳለው፣ ነገር ግን በሌሎች ላይ ጉልህ ተፅዕኖ (ከፍተኛ ጉዳት) በማያስከትል ትክክለኛ እና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ መደረግ እንዳለበት አፅንዖት ትሰጣለች።
የድንበር ተሻጋሪ ውኃ ጉዳዮች በተለይም ኤፍራጥስ እና ጤግሮስን በተመለከተ የሦስተኛ ወገኖች ጣልቃ ገብነት እና ሽምግልና ሳያስፈልግ በተፋሰስ ሀገራት መካከል ብቻ መፍትሔ ማግኘት እንዳለበት ጥብቅ አቋም ታራምዳለች።
እያንዳንዱ ድንበር ተሻጋሪ ወንዝ ራሱን የቻለ ቀጣናዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ታሪካዊ ባህሪያት ያሉት በመሆኑ ለአንድ አጠቃላይ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ተገዢ ከመሆን ይልቅ በተፋሰሱ ሀገራት ስምምነት መሠረት መተዳደር እንዳለበት ትከራከራለች።
በዚህ መርሕዋ መሠረትም ለኃይል ማመንጫ እና መስኖ በርካታ ግድቦችን ገንብታ እየተጠቀመችበት ሲሆን፣ በደቡብ ምሥራቅ አናቶሊያ ፕሮጀክቷ (GAP) እንደ አታቱርክ ያሉ ግዙፍ ግድቦችን ገንብታ ወደ ሥራ አስገብታለች።
ቱርኪዬ በ1997 የተመድ የዓለም አቀፍ የውኃ አጠቃቀም ስምምነትን በመቃወም ድምፅ ከሰጡ ሦስት ሀገራት (ቱርኪዬ፣ ቻይና እና ቡሩንዲ) አንዷ ስትሆን፣ ምክንያቷ ደግሞ "ዓለም አቀፍ ስምምነቱ የውኃ ሀብቴን እንዳልጠቀም በማገድ ሉዓላዊነቴን ይጥሳል" የሚል ነው።
የሦስትዮሽ ስምምነቶችን ብትቃወምም የሁለትዮሽ ትብብር እና ፕሮቶኮሎችን በተግባር ትደግፋለች። በተለይም በ1987 ከሶሪያ ጋር የተደረገው ፕሮቶኮል፣ ቱርኪዬ በየወሩ በአማካይ 500 ኪዩቢክ ሜትር የኤፍራጥስ ውኃ ለሶሪያ ለመልቀቅ ቃል የገባችበት ነው።
በቅርቡ ከኢራቅ ጋር የውኃ አያያዝን እና ትብብርን ለማሳደግ በተለይም እየተባባሰ የመጣውን ድርቅ ለመቋቋም የሚያስችል ረቂቅ የማዕቀፍ ስምምነት ላይ ደርሳለች።

የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት
ኢትዮጵያ ለዓባይ ውኃ ከ85 በመቶ በላይ ምንጭ የሆነች ሀገር ነች። ነገር ግን ለዘመናት በተደረገባት ጫና በዚህ የውኃ ሀብቷ ሳትጠቀም ቆይታለች።
በተለይም ግብፅ የቅኝ ግዛት ውሎችን እየጠቀሰች ዓለም አቀፍ ጫና መፍጠሯ ኢትዮጵያ በውኃ ላይ ለምትሠራው ማንኛውም ፕሮጀክት ድጋፍ እንዳታገኝ ስታደርግ ኖራለች።
የቅኝ ግዛት ውሎችን ስትቃወም የኖረችው ኢትዮጵያ ዓለም በሩን ቢዘጋባትም እጇን አጣጥፋ አልተቀመጠችም። መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን የመሠረት ድንጋይ አስቀምጣ ሥራውን ጀመረች።
ኢትዮጵያ ሕዳሴን ስትጀምር ግብፅ አንዳንዴ ፉከራ፣ አልሆን ሲላት ደግሞ ክስ ይዛ ዓለም አቀፍ ተቋማትን መዞር ጀመረች። በተለይም ኑክሌር ይመስል የውኃ ጉዳይን ከ10 ጊዜ በላይ ለተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ያቀረበችበት ሂደት በዓለም ታሪክ የመጀመሪያው ክስተት ነው።
ኢትዮጵያ ታላቁ ሕዳሴ ግድብን መገንባት ስትጀምር “እኔ በማመነጨው ወንዝ ሌላው ምን አገባው?” የሚል አቋም ይዛ አይደለም። ግብፅ እና ሱዳንን ጨምሮ ሌሎች የተፋሰሱ ሀገራትን አማክራ "የናይል ትብብር ማዕቀፍ ሥምምነት" ረቂቅን አቅርባ እንጂ።

የዓባይን ትርክት አዛብታ ለብቻዋ እንዳሻት ስትጠቀም የነበረችው ግብፅ ግን "የውኃዬን ጠብታ እንኳ የሚነካ ማንኛውንም አካል አልታገስም" ከሚለው ግልጽ ፉከራዋ፣ ኢትዮጵያን ሰላም የሚነሱ እጅ አዙር ድርጊቶች ውስጥ እስከ መሳተፍ የዘለቁ የክፋት መንገዶችን ስትከተል ቆይታለች።
በትክክለኛነት የተጀመረው ሕዳሴ ግን ተጠናቅቆ ተመርቋል። ግብፅ አሁንም ከዓረብ ሊግ እስከ አሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረት መዞሯን እና ኢትዮጵያ ላይም የፈሪ ዛቻዋን መንዛቷን ቀጥላለች።
"የናይል ትብብር ማዕቀፍ ሥምምነት" ከአሥር ዓመታት ድርድር በኋላ ከ11ዱ የተፋሰሱ ሀገራት ስድስቱ ሀገራት ፈርመውበት ወደ ተፈጻሚነት ገብቷል።

የማዕቀፉ ዓላማ ማንኛውም የተፋሰሱ ሀገር በዓባይ ላይ ለሚሠራው ፕሮጀክት በጋራ ስምምነት እንዲሆን ማመቻቸት ነው። ይህ ደግሞ በፕሮጀክቶቹ ምክንያት ጉልህ ጉዳት የሚደርስበት ሀገር ቢኖር እንኳን የማካካሻ ስትራቴጂ እንዲኖር የሚያመቻች በመሆኑ ለጋራ ብልጽግና መንገድ የሚከፍት ነው።
የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት ታዲያ ዓለም አቀፍ የውኃ ስምምነቶችን ማክበር እንዳለ ሆኖ ከቱርኪዬ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አስተዳደር ስትራቴጂ ሊማሩት የሚገባው ጉዳይ ይህን "የናይል ትብብር ማዕቀፍ ሥምምነት" ተግባራዊ ማድረግ ነው።
በለሚ ታደሰ