Search

አውስትራሊያ ከ16 ዓመት በታች ለሆኑ ሕፃናት ፈቃድ በሚሰጡ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ላይ የምትጥለውን የገንዘብ ቅጣት በዕጥፍ አሳደገች

እሑድ ሰኔ 21, 2018 52

በዚህ በቴክኖሎጂ ዘመን ሕፃናት በማህበራዊ ሚዲያ ምክንያት ለአዕምሮ ጤና ችግሮችና ለተለያዩ ጉዳቶች እየተዳረጉ መምጣታቸው ይታወቃል።

ይህንን አደገኛ አካሄድ ለማስቆም የተነሳችው አውስትራሊያ፣ አሁን ደግሞ ሕጉን በሚጥሱ የማህበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎች ላይ የምትጥለውን የገንዘብ ቅጣት በከፍተኛ ሁኔታ አሳድጋዋለች።

የመንግሥትን እገዳ ቸል በሚሉ ተቋማት ላይ ይጣል የነበረው ቅጣት ከ45 ሚሊዮን ወደ 99 ሚሊዮን የአውስትራሊያ ዶላር (ወደ 68 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር) ከፍ እንዲል ተደርጓል።

ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት በ10 ታዋቂ የማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ እንዳይገቡ ከታኅሣሥ 2025 ዓ.ም ጀምሮ እገዳ ብትጥልም፥ ታዳጊዎቹ ግን አሁንም መተግበሪያዎቹን በስፋት እየተጠቀሙባቸው እንደሆነ ተደርሶበታል።

በዚህም ምክንያት እንደ ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም፣ ስናፕቻት፣ ቲክቶክ እና ዩቲዩብ ባሉ ግዙፍ መድረኮች ላይ ጥብቅ ምርመራ ተጀምሯል።

በተሻሻለው አዲስ ሕግ መሠረት የአውስትራሊያ የኢ-ሴፍቲ ኮሚሽነር ሙሉ ሥልጣን የተሰጠው ሲሆን፣ የማህበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎቹ ሕፃናትን ለማገድ በትክክል ምን ዓይነት እርምጃዎችን እንደወሰዱ የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ እንዲያቀርቡ የማስገደድ መብት ይኖረዋል።

ይህ ጥብቅ እገዳ ተጠቃሚዎች ይዘት እንዲለጥፉና ማኅበራዊ መስተጋብር እንዲያደርጉ የሚፈቅዱ ሁሉንም መድረኮች የሚያካትት ሲሆን፤ ከዚህ በተጨማሪም ታዳጊዎች ያለገደብ በድረ-ገጾች ላይ እንዳይቀሩ የሚያግዱ ተጨማሪ መቆጣጠሪያዎች በሕጉ ውስጥ ተካተዋል።

ይህ እርምጃ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ትርፍ ላይ ብቻ ሳይሆን ለሕፃናት ደኅንነትም ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ያስገድዳቸዋል ተብሏል።

በልዩ እሸቱ