Search

በህገ-ወጥ የውጭ ምንዛሪ ወንጀል የተሰማሩ 123 ተጠርጣሪዎች የባንክ ሒሳብ ታገደ

ዓርብ መስከረም 09, 2018 187

በህገ-ወጥ የውጭ ምንዛሪ የወንጀል ተግባር ላይ የተሰማሩ 123 ተጠሪጣሪዎች የባንክ ሂሳብ እንዲታደግ መደረጉን የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት አስታወቀ።  

ህጋዊና መደበኛ የባንክ ስርዓትን ወደጎን በመተው በህገ-ወጥ እና ትይዩ ገበያ የውጭ ምንዛሪ ወንጀል ላይ የተሰማሩ አካላት ላይ እርምጃ መወሰዱ እና ሌሎች ላይ ደግሞ የተጠናከረ ክትትል እየተደረገ መሆኑ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት በቅርቡ መግለፁ ይታወሳል።

በዚህም መሠረት በተለያየ ደረጀ በህገ-ወጥ የውጭ ምንዛሪ የወንጀል ድርጊት ላይ የተሰማሩ የ123 ተጠርጣሪዎች የገንዘብ እንቅስቃሴ በዛሬው ዕለት ታግዶ የህግ ተጠያቂነት ለማረጋገጥ በሂደት ላይ እንደሚገኝ አገልግሎቱ ለኢቢሲ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

አገራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ በርካታ ሰው የውጭ ምንዛሪ አገልግሎትን በህጋዊ መንገድ እያካሄደ በመሆኑ በእጅጉ የሚበረታታ መሆኑም ተገልጿል።

ነገር ግን አንዳንድ አካላት አሁንም ከጥቁር ገበያ የውጭ ምንዛሪ የወንጀል ድርጊት ለማትረፍ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆናቸውን በክትትል መረጃዎች መረጋገጡም ነው የተጠቆመው። 

በተጨማሪም አንዳንድ የባንክ ባለሙያዎች በጥቁር ገበያ የውጭ ምንዛሪ የወንጀል ድርጊት ውስጥ ተሳትፎ ያላቸው መሆኑ የክትትል መረጃው ውጤት የሚያመላክት በመሆኑ ተጨማሪ ምርመራ በመደረግ ላይ እንደሚገኝ ተመላክቷል፡፡

#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #Financial_Intelligence_Service