በምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ኡጋንዳ፣ የቡና ምርታማነትን በማሳደግ ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ መጠን ከፍ ለማድረግ የሚያስችሉ ሰፋ ያሉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በአሁኑ ወቅት ቡና ከወርቅ በተጨማሪ ለኡጋንዳ ዋነኛ የገቢ ምንጭ ለመሆን ችሏል።
የሀገሪቱ ግብርና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፣ ባለፈው ጥቅምት ወር ብቻ ከ685 ሺህ ከረጢት በላይ የቡና ምርት ለውጭ ገበያ ቀርቧል። ይህም ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ለውጭ ገበያ ከተላከው 497 ሺህ ከረጢት ምርት ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ጭማሪ የታየበት መሆኑን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ገልጿል።
ሀገሪቱ ባለፈው ዓመት ብቻ ወደ ውጭ ከላከችው አጠቃላይ የቡና ምርት 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያገኘች ሲሆን፣ ይህ ዓመታዊ ገቢ ከአምና በፊት ከነበሩት ዓመታት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በዕጥፍ መጨመሩ ተጠቁሟል።
የኡጋንዳ ቡና አምራች ሕብረት ሥራ ማህበራት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሮበርት ብያሩሃንጋ እንደገለጹት፣ አርሶ አደሮች ከቡና ሽያጩ የተሻለ ገቢ ማግኘታቸው ሀገሪቱ ምርታማነቱን ለማሳደግ የያዘችውን እቅድ ለማሳካት አጋዥ ነው።
የቡና ምርታማነትንና የጥራት ደረጃን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት፣ የሀገሪቱ የግብርና ሚኒስቴር የተለያዩ በሽታዎችንና ተባዮችን የሚቋቋሙ የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች ለዓመታት በነፃ ሲያከፋፈል ቆይቷል።
በአውሮፓና በእስያ የቡና ምርት ፍላጎት መጨመሩም ኡጋንዳ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን የቡና አቅራቢነት ሚና እንድታጠናክር መልካም አጋጣሚ ፈጥሮላታል።
የዓለም አቀፍ ንግድ ባለሙያዋ ጃኔ ናሉንጋ በበኩላቸው፥ ቻይና የአፍሪካ ምርቶች ከቀረጥ ነፃ ሆነው ወደ ሀገሪቱ ገበያ እንዲገቡ የሰጠችው ፈቃድ ኡጋንዳ አማራጭ የገበያ ዕድል እንድታገኝ ያደረገ በመሆኑ፣ ቡናን በጥራትና በብዛት ለማቅረብ ትልቅ ዕድል መሆኑን አስረድተዋል።
በኡጋንዳ የቡና ምርታማነት እንዲያድግ የመንግሥትና የአርሶ አደሮች ጥረት እንዳለ ሆኖ፣ በዘርፉ የተሰማሩ የግል ባለሀብቶች ቁጥር መጨመርም የራሱን ድርሻ አበርክቷል።
ይሁን እንጂ ዘርፉ አሁንም ድረስ ፈተናዎች ተደቅነውበታል። በተለይም ከሦስት ሳምንታት በኋላ ተግባራዊ የሚደረገው የአውሮፓ ኅብረት የደን ጥበቃ መመሪያ (EUDR) በኡጋንዳውያን ቡና ላኪዎች ላይ ስጋት ፈጥሯል።

ይህ መመሪያ እያንዳንዱ ቡና ላኪ ድርጅት ምርቱ ከማሳ ላይ ተመርቶ ለገበያ እስኪቀርብ ድረስ ያለው ሂደት በአካባቢና በደን ሀብት ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት አለማድረሱን የሚያረጋግጥ ማስረጃ እንዲያቀርብ ያስገድዳል።
የኡጋንዳ ቡና ላኪዎች ግን ይህን ጥብቅ መመሪያ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ዝግጅት እንደሌላቸው እየገለጹ ይገኛሉ።
የኡጋንዳ መንግሥት በበኩሉ የአውሮፓ ኅብረት ያወጣው የጥራት ደረጃ ማስጠበቂያ መመሪያ ሀገሪቱ ቡናን በብዛትና በጥራት ለማምረት ከያዘችው እቅድ ጋር የሚጣጣም መሆኑን ገልጿል።
በተጨማሪም ሀገሪቱ ቡናን በጥሬው ከመላክ ይልቅ በሀገር ውስጥ ለማቀነባበርና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በትኩረት እንደምትሠራ አስታውቋል። ይህ እቅድ ኡጋንዳ የአፍሪካ የቡና ምርት ማቀነባበሪያ ማዕከል እንድትሆንና ከዘርፉ በላቀ ሁኔታ እንድትጠቀም የሚያስችላት መሆኑን ሮበርት ብያሩሃንጋ አክለው ገልጸዋል።
የሲጂቲኤን ዘገባ እንደሚያመለክተው፣ ኡጋንዳ በቀጣዮቹ 4 ዓመታት ውስጥ ማለትም እ.አ.አ እስከ 2030 ወደ ውጭ የምትልከውን የቡና ምርት መጠን በዓመት 20 ሚሊዮን ከረጢት ለማድረስ ትልቅ ግብ ይዛ እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች።
በመሀመድ ኢብራሂም
#ebcdotstream #EBC #Coffee #Production