Search

ኢትዮጵያ ታከናውናለች፡- የሌማት ትሩፋት ከምግብ ዋስትና እስከ ሥራ ዕድል ፈጠራ

ሓሙስ ሰኔ 18, 2018 49

ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ማክሮ-ኢኮኖሚዋን ለማረጋጋት እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በርካታ ሀገራዊ ንቅናቄዎችን ቀርጻ ስትተገብር ቆይታለች።

ከእነዚህም መካከል በገጠርም ሆነ በከተማ ማኅበረሰብ ውስጥ ከፍተኛ መነቃቃትን የፈጠረው ሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር አንዱ ነው።

በምግብ ራስን ለመቻል፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ለመቅረፍ እና የሀገር ውስጥ ምርትን በማሳደግ የውጭ ምንዛሪን ለማዳን ያለመ ስትራቴጂያዊ ዕቅድ የሆነው የሌማት ትሩፋት ንቅናቄው፣ በዋናነት የእንስሳት፣ የዶሮ፣ የንብ እና የዓሣ ምርት ላይ በማተኮር ሲተገበር ቆይቷል። ይህም በተለይ በከተማ ግብርና እና በገጠር አነስተኛ አምራቾች ዘንድ ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል።

የወተት እና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርት እንዲያድግ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያደረገ የሚገኘው የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብሩ፣ በዘመናዊ መንገድ የተደራጁ የላም ማለቢያ ማዕከላትን በመፍጠር የነፍስ ወከፍ የወተት አቅርቦት በከፍተኛ ሁኔታ አንድጨምር አድርጓል። ይህም ቀደም ሲል ለሕፃናት የሚሆን የወተት ምርት እጥረት በነበረባቸው አካባቢዎች ላይ ትልቅ እፎይታ ሰጥቷል።

በተመሳሳይ በከተሞች እና በገጠር መንደሮች የዶሮ እርባታን በቤተሰብ ደረጃ ማላመድ ያስቻለው መርሐ ግብሩ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የዶሮ ጫጩቶች ለአርሶ አደሩ እና ለከተማ ነዋሪው ተደራሽ በመደረጋቸው የእንቁላል እና የዶሮ ሥጋ አቅርቦት ገበያውን ማረጋጋት ጀምሯል።

ዘመናዊ የንብ ቀፎዎችን በማሰራጨት የማር ምርት ጥራት እና መጠን እንዲጨምር ተደርጓል። በሌላ በኩል ሰው ሠራሽ የዓሣ ኩሬዎችን በመቆፈር በተለይም የወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሪያ እንዲሆን ተደርጓል።

መርሐ ግብሩ በማኅበረሰቡ የዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ ያሳደረው አዎንታዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ለዓመታት አሳሳቢ የነበረውን የሕፃናት መቀጨጭ እና የምግብ እጥረት ለመቅረፍ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።

የእንቁላል፣ የወተት እና የሥጋ ምርቶች በየጓሮ መመረታቸው የተመጣጠነ የምግብ አቅርቦትን ቀላል አድርጎታል።

የሌማት ትሩፋት ሥራዎች ብዙ ካፒታል እና ሰፊ መሬት የማይጠይቁ በመሆናቸውም ሴቶች እና ወጣቶች በቤታቸው እና በጓሯቸው ሠርተው ገቢ የሚያገኙበት ሰፊ ዕድል ፈጥሯል። ይህም የኢኮኖሚ ጥገኝነትን ከመቀነስ ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከት ችሏል።

መርሐ ግብሩ ሀገራችን ካለችበት የማክሮ-ኢኮኖሚ ጫና እና የኑሮ ውድነት አንጻር፣ ዜጎች የዕለት ተዕለት የምግብ ፍጆታቸውን ከገበያ ከመግዛት ይልቅ ከራሳቸው ጓሮ እንዲያሟሉ በማድረጉ የኑሮ ጫናውን በተወሰነ መልኩ አቅልሏል።

በሌላ በኩል፣ ኢትዮጵያ በምግብ ምርቶች ላይ የነበረባትን የውጭ ጥገኝነት ለመቀነስ እና የሸማችነት ባህልን ወደ አምራችነት ለመቀየር እንደ ትልቅ መሣሪያ አገልግሏል።

በመሆኑም የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብሩ ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል እና የድህነት ቅነሳ ስትራቴጂዋን ለማገዝ የያዘችው ትክክለኛ እና ተስፋ ሰጪ መንገድ ሲሆን፣ ባለፉት ዓመታት የተሠሩት ሥራዎችም አቅም መኖሩን ያሳዩ እና የዜጎችን አምራችነት ያረጋገጡ ናቸው።

በአድማሱ አራጋው