Search

በድሬዳዋ አስተዳደር የፌዴራል ልዩ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ ተጀመረ

ሓሙስ ሰኔ 18, 2018 66

በትምህርት ሚኒስቴር ሙሉ ወጪ በድሬዳዋ ከተማ የሚገነባ የፌዴራል ልዩ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ ተጀምሯል።

የትምህርት ቤቱን ግንባታ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር በይፋ አስጀምረዋል።

ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በዚሁ ወቅት፣ መንግሥት የተሻለ የትምህርት ጥራትና የላቀ የትምህርት ከባቢ ለመፍጠር የተመረጡ ተማሪዎች የሚማሩባቸውን የፌዴራል ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች በተለያዩ አካባቢዎች እየገነባ መሆኑን ገልጸዋል።

ዛሬ ግንባታ የተጀመረው ትምህርት ቤትም እንደ ሀገር በብቃታቸው የተመረጡ ተማሪዎችን በመቀበል የሚያስተምር ሲሆን፣ ግንባታው በአንድ ዓመት ውስጥ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም የፌዴራል ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን የማስፋፋት ሥራ እንደሚቀጥል ገልጸው፣ በባሕር ዳር፣ አርባምንጭ እና አሶሳ ተመሳሳይ የልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ግንባታ በቅርቡ እንደሚጀመር አስታውቀዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር በበኩላቸው፣ ትምህርት ሚኒስቴር ለከተማዋ እድገትና ለትውልድ ግንባታ እያደረገ ላለው አስፈላጊ ድጋፍ ምስጋና አቅርበው፣ ፕሮጀክቱ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ፣ የላቀ ችሎታ ያላቸውን ተማሪዎች ለማብቃት እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሰው ሀብት ለመፍጠር እየተተገበሩ ካሉ የሪፎርም ተግባራት ውስጥ አንዱ መሆኑን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።