ሕወሓት አሁንም የትግራይን ወጣቶች ወደ አዲስ ጦርነት ለመማገድ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ወታደራዊ አማካሪ እና የተኩስ አመራር ኃላፊ ጄኔራል ዓለምሸት ደግፌ ገልፀዋል።
በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ለታዩት የጸጥታ ችግሮች ዋነኛው ምክንያት "ፅንፈኝነት" መሆኑን በመድረኩ ላይ አስገንዝበዋል።
ጄኔራል ዓለምሸት ደግፌ ባደረጉት ንግግር ባለፉት ዘመናት የአክራሪ ልሂቃን "የእኔ ብቻ" የሚል ጽንፈኛ አስተሳሰብ ወጣቶች ሕይወታቸውን እንዲከፍሉ፣ ሀገር እንድትደማ እና የሀገር ሀብት ለልማት ሳይሆን ለጦርነት እንዲውል ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል።
"ፅንፈኛው ልሂቅ ከየትኛውም ብሄር ይምጣ፣ ከራሱ የሥልጣን ፍላጎት ውጭ ለሕዝብ ደኅንነት፣ ለሀገር ዕድገት እና ለሉዓላዊነት ክብር የማይሰጥ ኃይል ነው" ብለዋል ጄኔራል ዓለምሸት፡፡
አክለውም እነዚህ ኃይሎች ከውጭ ጠላቶች ጋር ጭምር በመጣመር የራሳቸውን ፍላጎት በሕዝብ ላይ ለመጫን እና የደም መፋሰስ ሂደት እንዲቀጥል እያደረጉ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የሕወሓት ቡድን በአሁኑ ወቅት በሕዝብ ላይ የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ እያካሄደ እንደሚገኝ እና ልክ ከአምስት ዓመት በፊት ያደርገው እንደነበረው ሁሉ ዳግመኛ እየፎከረ መሆኑን ገልጸዋል።
የቀድሞው የጦርነት ጠባሳ ሳይበቃው አሁንም የትግራይን ወጣቶች ወደ ጦርነት ለመማገድ እየተዘጋጀ መሆኑን ያመለከቱት ጄኔራል ዓለምሸት፣ ለዚህ እኩይ ዓላማውም ከሀገር ውስጥ እና የውጭ ፀረ ሰላም ኃይሎች ጋር ችግር ለመፍጠር በዝግጅት ላይ መሆኑን ይፋ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ ልሂቃን ከዚህ ጥፋት ሀገራችንን ለመታደግ የመፍትሄው አካል ሊሆኑ እንደሚገባ ጄኔራል ዓለምሸት ደግፌ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል ።
በወንደሰን አፈወርቅ