የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሔደው 28ኛ መደበኛ ጉባኤው የፌዴራል ሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አጽድቋል።
የሕግ እና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እፀገነት መንግሥቱ የፌዴራል የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅን ሪፖርት እና የውሳኔ ሐሳብ በዝርዝር አቅርበዋል።
ረቂቅ አዋጁ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 34 ንዑስ አንቀጽ (5) መሠረት እንዲሁም አንቀጽ 78 (5) መሠረት የግል እና የቤተሰብ የሕግ ጉዳዮችን አስመልክቶ የሚነሡ አለመግባባቶችን በፈቃደኝነት ላይ በተመሠረተ ሁኔታ በሃይማኖታዊ ሕጐች ለመዳኘት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
ሰብሳቢዋ አክለውም፣ ረቂቅ አዋጁ የፌዴራል ሸሪዓ ፍርድ ቤቶች እንደ አንድ የሀገራችን የፍትሕ አካል የዳኝነት ነጻነታቸው ተጠብቆ እና ተጠያቂነት የሰፈነበት አሠራር የሚያሰፍን ቀልጣፋ እና ተደራሽነት ያለው የዳኝነት አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን አንሥተዋል።
ረቂቅ አዋጁ ሃይማኖታዊ እሴቶችን የሚያከብር፣ ከኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት ጋር የማይቃረን እና ረቂቅ አዋጁ የፍርድ ቤቶቹን ተጠሪነት፣ አደረጃጀት እና የፌዴራል ሸሪዓ ፍርድ ቤቶች አስተዳደር ጉባዔን የሚያቋቁም እንደሆነ ጨምረው አንሥተዋል።
የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው፣ ረቂቅ አዋጁን ለማዳበር የተዘጋጁት መድረኮች አሳታፊ እንደነበሩ አስተያየት ሰጥተዋል።
በመጨረሻም፣ ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጁ ላይ ሰፊ ውይይት ካደረገ በኋላ፣ የፌዴራል ሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ፣ አዋጅ ቁጥር 1428/2018 አድርጎ በሙሉ ድምፅ ማፅደቁን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።