Search

የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ለከተማ ትራንስፎርሜሽን ምርጥ ተሞክሮ ነው - ኦብሰርቨር ሪሰርች ፋውንዴሽን

ሓሙስ ሰኔ 18, 2018 63

 

የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የኮሪደር ልማት ሥራዎች የዜጎችን የኑሮ ጥራት ማዕከል ያደረገ የከተማ ትራንስፎርሜሽን ምርጥ ተሞክሮ መሆኑን ኦብሰርቨር ሪሰርች ፋውንዴሽን የተሰኘው ዓለም አቀፍ የጥናት ተቋም አረጋግጧል።

ኢትዮጵያ በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች እያከናወነች ያለው የኮሪደር ልማት እንዲሁም የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራዎች የዜጎችን የዕለት ተዕለት ሕይወት በተጨባጭ የለወጡ ውጤት ተኮር ስኬቶች ናቸው።

ከልማቱ ጋር ተያይዞ ከቀደመ ቀያቸው የተነሡ ዜጎች አብሮነታቸው ሳይናጋ፣ ትምህርት ቤቶችን፣ የመጫወቻ እና የመዝናኛ ስፍራዎችን እንዲሁም የንግድ ቦታዎችን ያካተቱ ዘመናዊ መሠረተ ልማቶች በተሟሉላቸው መንደሮች እንዲሰፍሩ መደረጉ የዜጎችን የኑሮ ጥራት ማዕከል ያደረገ የልማት ማሳያ መሆኑ ተረጋግጧል።

ይህ በከተሞች የተመዘገበው ስኬት በአሁኑ ወቅት የአርሶ አደሩን ሕይወት በተጨባጭ ለመቀየር በገጠር የኮሪደር ልማትም እየተደገመ ይገኛል።

በኢትዮጵያ በተግባር የታየው ሁለንተናዊ የልማት ስኬት በአዳጊ ሀገራት የሚገነቡ ታላላቅ መሠረተ ልማቶች በቢሮክራሲ እና በወጣው የገንዘብ መጠን ሳይሆን፣ በዜጎች ምቾት ሊገመገሙ እንደሚገባ ይፋ ከተደረገ አዲስ ዓለም አቀፍ ጥናት ጋር ቀጥተኛ ትሥሥር እንዳለው ተመላክቷል።

መቀመጫውን በሕንድ ያደረገው ኦብሰርቨር ሪሰርች ፋውንዴሽን ይፋ ባደረገው ጥናት መሠረት፣ እንደ ሙምባይ፣ ሳኦ ፖሎ፣ ጆሃንስበርግ እና ጃካርታ ያሉ የብሪክስ አባል ሀገራት ከተሞች በአሁኑ ወቅት የትራፊክ መጨናነቅ፣ የቤት እጥረት እና የአየር ብክለት በጋራ እየፈተናቸው ይገኛል።

በመሆኑም የመንግሥት የኦዲት እና የክትትል ሥርዓት ከባህላዊ የሕግ አከባበር ቁጥጥር ወጥቶ፣ ኢትዮጵያ እየተገበረች እንዳለው ዓይነት የነዋሪዎችን ምቾት ወደሚያረጋግጥ ግምገማ መሸጋገር እንዳለበት ትንተናው ያሳያል።

ጥናቱ እንደሚያመለክተው፣ በተለመደው አሠራር አንድ ትልቅ ፕሮጀክት በግዥ ሕጉ መሠረት ስለተከናወነ ብቻ ስኬታማ ሊባል አይችልም። ዋናው መመዘኛ መሆን ያለበት ፕሮጀክቱ የነዋሪዎችን የእንግልት እና የጉዞ ጊዜ በተጨባጭ ማቃለል መቻሉ ላይ ነው።

ለዚህም ማሳያ የሚሆነው እንደ ብራዚል፣ ቻይና እና ብሪታንያ ያሉ ሀገራት የክትትል ሥርዓታቸውን ከድህነት ቅነሳ፣ ከትራንስፖርት ቀልጣፋነት እና ከአየር ንብረት መቋቋም ጋር ማያያዝ መጀመራቸው ነው።

በመሆኑም የብሪክስ አባል ሀገራት ከተሞች ከባህላዊ እና መደበኛ የሁለትዮሽ ጉብኝቶች ወጥተው፣ ኢትዮጵያ በከተማ እና በገጠር የኮሪደር ልማት ካስመዘገበችው ተጨባጭ ውጤት ተኮር የልማት አጋርነት ምርጥ ተሞክሮ መውሰድ እንዳለባቸው የኦብሰርቨር ሪሰርች ፋውንዴሽን ጥናት አስገንዝቧል።

በሰለሞን ገዳ