80 ዓመታትን በከፍታ እየበረረ ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ኩራት ነው፡፡ አየር መንገዱ በዚህ ደረጃ ከፍታው ላይ እንዲቆይ ካደረጉአቸው ጉዳዮች መካከል ራዕይ ያለው አመራር ነው፡፡
ሩቅ አስቦ የተመሰረተው አየር መንገዱ የተሟላ አመራር እንዲፈጥር ካደረጉት ከፍሎቹ መካከል የአቪየሽን ዩንቨርሲቲው ከቀዳሚዎቹ መካከል ነው፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከኢትዮጵያ አልፎ እስከ መካከለኛው ምሥራው ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት በአቪየሽን ኢንዱስትሪው ላይ የራሱን አሻራ እያኖረ 60 ዓመታትን ተሻግሯል፡፡
የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ በአፍሪካ ትልቁ እና ቀዳሚ የአቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ ነው። ከትንሽ የሥልጠና ክፍል ዓለም አቀፍ ደረጃውን ወደጠበቀ ዩኒቨርሲቲ የተሸጋገረበት ሂደት ደግሞ የአየር መንገዱን ኢትዮጵያዊነት መልክ ማሳያ ነው።
ዩኒቨርሲቲው ከኢትዮጵያ አየር መንገዱ 8 ስትራቴጂክ የቢዝነስ ዩኒቶች አንዱ ሲሆን፣ በየዓመቱ ከ4 ሺህ በላይ ሠልጣኞችን የመቀበል አቅም ያላቸው አምስት ትምህርት ቤቶችም አሉት።
ዩኒቨርሲቲው በማሰልጠኛ ደረጃ ሲመሰረት ዓላማ አድርጎ የተነሳው የኢትዮጵያ አየር መንገድን መምራት የሚችል ብቁ የሰው ኃይል ማፍራትን ነበረ።

በ"ራዕይ 2025" የቦይንግ B100 እና A787 ምስለ በረራ (simulators) ጨምሮ፣ የመማሪያ ክፍል ሕንጻዎችን እና ማደሪያ ክፍሎች ለማዘመን ከ350 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ አድርጓል።
የካቲት 27 ቀን 2015 ዓ.ም አካዳሚው በይፋ ወደ ኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ የተሸጋገረበት ታሪካዊ ዕለት ነው። ሽግግሩ ተቋሙ ከሙያ ሰርተፍኬት እና ዲፕሎማ አልፎ ሙሉ የቅድመ ምረቃ እና የድህረ ምረቃ ዲግሪዎችን እንዲሰጥ አስችሎታል። ይህም በ‘ኤሮስፔስ’፣ ቴክኖሎጂ፣ በቴክኒክ ክህሎቶች እና በአካዳሚያዊ ምርምር መካከል ያለውን ልዩነት ለማስተካከል ጠቅሞታል።
ዩኒበርሲቲው በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣንም ዕውቅና ተሰጥቶታል፡፡ ከዓለም አቀፉ የሲቪል አቪየሽን ድርጅት (ICAO) የቀጣናው የሥልጠና ማዕከልነትን ዕውቅና አግኝቷል፡፡
በአውሮፓ አቪዬሽን ደኅንነት ኤጀንሲ (EASA) በክፍል 147 የB737 እና B757/767 የጥገና ማሠልጠኛ ተቋምነት ማረጋገጫ አለው፡፡ በዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር (IATA)ም ማረጋገጫ ተሰጥቶታል፡፡
ዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር (IATA) የቀጣናዊ የሥልጠና አጋር ነው፡፡ በዓለም አቀፍ የአቪየሽን ማሰልጠኛ ተቋማት በተደረገ ምዘናም ከፍተኛ ደረጃ ያገኘ ተቋም ነው፡፡
ከስድስት አሥርት ዓመታት በላይ እድሜ ያለው የኢትዮጵያ አቪየሽን ዩኒቨርሲቲ በቀጣናው ትልቁ እና ዘመናዊ የበረራ እና ቴክኒክ ማሰልጠኛ ማዕከል ሲሆን፣ ምርጥ እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን የታጠቀ ነው።
የምስለ በረራ (simulator) ቴክኖሎጂ ፕሮግራምን በማስተዋወቅ እና በተሳካ ሁኔታ በመቀም ላይ ከሚገኙ ጥቂት የአፍሪካ የአቪየሺን የሥልጠና ማዕከላትም የመጀመሪያው ነው።
በአፍሪካ ደረጃ በፍጥነት በማደግ ላይ ያለው እና ትልቁ የአቪየሽን ዩኒቨርሲቲ ተግባራዊ እና የሥራ ላይ ሥልጠናዎችን ለመስጠት የሚያስችሉ ዘመናዊ አውሮፕላኖች፣ የማሠልጠኛ መሣሪያዎች እና የጥገና ተቋማት ባለቤት ነው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የሥልጠና መስፈርት ያሟላው የኢትዮጵያ አቪየሽን አካዳሚ ሠልጣኞቹን በከፍተኛ ደረጀ የሚያበቁ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን የታጠቀ ነው፡፡ በዚህም በዓለም አቀፍ እና በአፍሪካ ደረጃ ከፊት ከሚሰለፉት ብቁ ተቋማት አንዱ በመሆኑ የብዙዎች ምርጫ ነው፡፡

በአፍሪካ፣ በአውሮፓ እና በመካከለኛው ምሥራቅ ከሚገኙ ከ52 በላይ ሀገራት የመጡ በሺህዎች የሚቆጠሩ የአውሮፕላን ባለሙያዎችን አሠልጥኖ አብቅቷል።
በ1964 ዓ.ም የአብራሪዎች ማሠልጠኛ፣ በ1967 የአውሮፕላን ጥገና ቴክኒሽያን፣ በ1981 ደግሞ የማርኬቲንግ እና የፋይናንስ ትምርት ቤቶች ሥራ እንደጀመሩ ከአየር መንገዱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
የፓይለቶች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤቱ ባለፉት 61 ዓመታት ውስጥ በመላው አፍሪካ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በእስያ እና በአውሮፓ ከሚገኙ 52 ሀገራት የተውጣጡ አብራሪዎችን በብቃት አሰልጥኖ ወደ ሥራ አሰማርቷል።
ትምህርት ቤቱ በአሁኑ ወቅት ባለብዙ ሞተር ደረጃ መሣሪያዎች (CPL/IR/ ME) እና በምስለ በረራ ለንግድ የፓይለትነት ፈቃድ እውቅና ያላቸው የሥልጠና ፕሮግራሞች አሉት። በተጨማሪም ለአብራሪ አሰልጣኞች፣ ለበረራ ስምሪት ባለሙያዎች እና ምስለ በረራ አሠልጣኞች ሥልጠናዎችን ይሰጣል።
ከኢትዮጵያ አየር መንገድ 8 ስትራቴጂክ የቢዝነስ ዩኒቶች ውስጥ የኢትዮጵያ አቪየሽን አካዳሚ አንዱ ሲሆን፤ የዓለም አቀፍ ደንበኞች አገልግሎት፣ የሆቴልና ቱሪዝም አስተዳደር፣ የሀገር ውስጥና ቀጣናዊ አገልግሎት፣ የካርጎ እና ሎጂስቲክስ አገልግሎት፣ የጥገና እና ቴክኒክ አገልግሎት፣ የበረራ ላይ መስተንግዶ አገልግሎት፣ የአውሮፕላን ማረፊያዎች ቁጥጥር አገልግሎት የአየር መንገዱ ሌሎቹ የቢዝነስ ዩኒቶች ናቸው፡፡
አካዳሚው ቀድሞ የነበረውን ሰዓት ላይ የተመሠረተ የሥልጠና ሥርዓት በመቀየር በብቃት ላይ የተመሠረተ ሁለገብ ሥልጠና እየሰጠ ነው፡፡ ሠልጣኞች በተለያዩ የአውሮፕላኖች ላይ ሥልጠና የሚወስዱ ሲሆን፣ ሲሙሌተር እና ትክክለኛ አውሮፕላንን በመጠቀም ሁለገብ ብቃት የሚያጎናጽፋቸውን ክህሎት እንዲያገኙ ይደረጋሉ፡፡
እየጨመረ የመጣውን በበረራ ወቅት የሚያጋጥሙ ከቁጥጥር ውጭ የሆኑ አደጋዎችን ለመከላከል የበረራ ከቁጥጥር ውጭ መሆንን መከላከል እና ሲከሰትም በአግባቡ የማስተዳደር (UPRT) ሥልጠናም ይሰጣል፡፡
የአውሮፕላን ጥገና ትምህርት ቤቱ ከመደበኛው ሥልጠና በተጨማሪ አጫጭር የተግባር ሥልጠናዎችንም ይሰጣል። ይህ ሥልጠና የዘመናዊ የአውሮፕላን ጥገና ሥልጠናዎችን ሙሉ ለሙሉ የሚሸፍን ነው። በየጊዜው የሚለዋወጠውን የአቪየሽን ቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም የንድፈ-ሐሳብ እና ተግባራዊ ሥልጠናውን ሚዛናዊ በማድረግ ብቁ ባለሙያዎችን በማፍራትም ይታወቃል፡፡

የስምሪት ባለሙያዎች ሥልጠና የበረራ ዝግጅትን ቁጥጥር እና ክትትል፣ የበረራ መረጃ አያያዝ፣ የኦፕሬሽንና የአየር ትራፊክ አገልግሎት (ATS) የበረራ እቅድ ዝግጅት እና የበረራ ላይ ግንኙነትን ያካተተ ነው፡፡
የካቢን ሠራተኞች ማሰልጠኛ ማዕከል ለዓመታት ጥራቱን የጠበቀ ሙያዊ ሥልጠና እየሰጠ ያለ ግንባር ቀደም ትምህርት ቤት ነው፡፡ ይህ የማሠልጠኛ ማዕከል ከ58 ለሚበልጡ ዓመታት በከፍተኛ ደረጃ ጥራቱን የጠበቀ እና ሥነ-ምግባር ላይ የተመሰረተ ሥልጠናን በመስጠት በኢንዱስትሪው ውስጥ ከፍተኛ ዝና አትርፏል።
የኮሜርሺያል እና ግራውንድ ኦፕሬሽንስ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት በአውሮፕላን ማረፊያ እና በካርጎ ሥራ ላይ መሳተፍ ለሚፈልጉት ሀሉ ሥልጠና ይሰጣል። የሥልጠናው ዋና ዓላማ ሠራተኞች አጠቃላይ ደንቦችን እንዲያውቁ የሚያስችል ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ አቪየሽን ባለ ሥልጣን እና ከዓለም አቀፍ የአቪየሽን ባለሥልጣናት ደረጃዎች ጋር የሚናበቡ ጥልቀት ያላቸው የሥልጠና ፕሮግራሞችን ያካሄዳል። ሠልጣኞቹ ሁሉንም ተያያዥ ፖሊሲዎች፣ አሠራሮች እና የትግበራ ሂደቶችን የተመለከቱ መረጃዎችን እና መመሪያዎችን የሚያገኙት ፈቃድ ካላቸው መምህራን ሲሆን፣ ሥልጠናውን በብቃት ካጠናቀቁ የምስክር ወረቀት ያገኛሉ።
አካዳሚው የአየር መንገዱ ከፍተኛ አመራሮች ይበልጥ ኃላፊነት የሚሰማቸው እንዲሆኑ ለማድረግ የሚያስችል የአቅም ግንባታ ሥልጠናም እየሰጠ ነው። የሰው ኃይል ልማት ፕሮግራሙ (MDP) አየር መንገዱ በአፍሪካ ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ አመራር እንዲኖረው አስችሏል።
ሠልጣኞቹ ትርፍ ሰዓታቸውን የቅርጫት ኳስ በመጫወት፣ የቤት ውስጥ ስፖርቶች፣ በጂም ውስጥ አካላዊ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ እንዲሁም በአካዳሚው ውስጥ ባሉ ጽዱ አካባቢዎች በመንሸራሸር በደስታ ያሳልፋሉ።
61ኛ ዓመቱን እያከበረ ያለው አካዳሚው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጀርባ አጥንት ነው፡፡ ከዚያም አልፎ በርካታ የአፍሪካ እና የመካከለኛ ምሥራቅ የአቪየሺን ባለሙያዎችን አሰልጥኖ ማብቃት የቻለ ነው፡፡ በቀጣይም የዘርፉን የሰው ኃይል ፍላጎት ለማሟላት ከዘመኑ ጋር የሚራመድ ሥልጠና መስጠቱን ይቀጥላል፡፡
በለሚ ታደሰ