በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው 8ኛው ዓለም አቀፍ "አግሮ ፉድ እና ፕላስትፕሪንትፓክ ኢትዮጵያ" እንዲሁም በ2ኛው "የኢትዮጵያ የምግብ እና የቡና ንግድ ትርኢት" ላይ ለመሳተፍ ከመላው ዓለም የመጡ ባለሀብቶች የኢንዱስትሪ መሪዎችና የዘርፉ ተዋናዮች በመዲናዋ የሚገኙ ታዋቂ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ጎበኙ።
ጉብኝታቸውን ያደረጉት እንግዶች በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙትን የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች፣ የወንዝ ዳር ልማት ስራዎችን እንዲሁም የከተማዋን ውብ የቱሪዝም መዳረሻዎች ተመልክተዋል።
በጉብኝታቸው ወቅት ተሳታፊዎቹ በከተማዋ በአጭር ጊዜ ውስጥ በተከናወኑ የልማት ስራዎች መደነቃቸውን ገልጸዋል።
በተለይም አዲስ አበባ ለኮንፍረንስ ቱሪዝም ያላትን ምቹ መሠረተ ልማት እና ዘመናዊ ገጽታ ያደነቁት እንግዶቹ፣ ከተማዋ ለወደፊት የሚያዘጋጇቸው የንግድ ትርኢቶች ቀዳሚ ምርጫቸው እንደምትሆን ማረጋገጣቸውን ከአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።