ከተሞች የሥልጣኔ መናኻሪያና የኢኮኖሚ ሞተሮች ቢሆኑም፣ አብዛኛውን ጊዜ ከተፈጥሮ ሥነ-ምህዳር ጋር ያላቸው ግንኙነት የተቋረጠ ነው።
በተለይም በፈጣን የከተማ ዕድገት ውስጥ የሚያልፉ ታዳጊ ከተሞች፣ የተፈጥሮ ውኃ አካላትን ለቆሻሻ ማከማቻነትና ለደኅንነት ሥጋትነት አሳልፈው ይሰጣሉ።
አዲስ አበባም ለብዙ አሥርት ዓመታት በዚህ አስከፊ አዙሪት ውስጥ ስትማቅቅ ቆይታለች።
ሆኖም፣ አሁን ፍሬ እያፈራ ያለው የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት፣ ወንዞችን ከብክለት አላቅቆ ወደ ከተማዋ ዋነኛ የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና ቱሪዝም ማዕከልነት የመለወጥ ስትራቴጂካዊ ፍልስፍናን ይዟል።
ከተሸሸገ ጨለማ ወደ ብሩህ የሕዝብ መናፈሻ
ከእንጦጦ አናት ተነሥቶ እስከ ፒኮክ የሚዘልቀውን ልማት ለታዘበ፣ የቀድሞውና የዛሬው እውነታ ሰማይና ምድር ናቸው።
ቀደም ሲል የሚሸቱ፣ መርዛማና ሕገ-ወጥ ድርጊቶች ይፈጸሙባቸው የነበሩት ሥፍራዎች ዛሬ ማራኪ የተፈጥሮ መዝናኛዎች ሆነዋል።
ይህም የነዋሪዎችን የዕይታ ለውጥ በማምጣት መስታወት ሳይዘጉ ማለፍ በማይቻልበት ቦታ፣ አሁን ቤተሰብን ይዞ መዝናናት፣ ንጹሕ አየር መተንፈስና ልጆችን ማጫወት ተችሏል።
እንዲሁም በትራንስፖርት መጨናነቅ ፈንታ፣ ነዋሪዎች በማራኪ የእግር መንገዶች አዕምሯቸውን እያደሱ ለመጓዝ ችለዋል። በተጨማሪም ለአረጋውያን ድሮ ይዋኙባቸው የነበሩ ንጹሕ ወንዞች ታክመው ተመልሰው በማየታቸው የድሮዋን አዲስ አበባ ያገኙ ያህል ጥልቅ ስሜት ፈጥሮባቸዋል።
የልማቱ ስትራቴጂያዊ ምሰሶዎች
የሥነ-ምህዳር መታደግ - ጥቁር ውኃን ማከም፣ ቆሻሻን ማጣራትና ተፈጥሮን ወደ ነበረችበት መመለስ።
የጤና ኢንቨስትመንት - ዜጎች በነፃነት የሚንቀሳቀሱባቸውና ስፖርት የሚሠሩባቸውን ክፍት ቦታዎች መፍጠር።
ማኅበራዊ ትስስር - ዜጎች በመገናኘት አብሮ የመኖር ባህልና መተሳሰብን ማሳደግ።
የኢኮኖሚ ሽግግር - ዋጋ አልባ የነበሩ ስፍራዎችን ወደ ቱሪስት መዳረሻ፣ ዘመናዊ ሪል እስቴቶችና የሆቴሎች የኢኮኖሚ ቀጣና መቀየር።
የዓለም ሀገራት ተሞክሮዎች
ወንዞችን ማከም እና መለወጥ በዓለም የተፈተነ ስኬታማ ስትራቴጂ ነው። ደቡብ ኮሪያ በ20ኛው ክፍለ ዘመን በዋና ከተማዋ በኮንክሪት እና በመኪና መንገድ ተሸፍኖ የነበረውን ቼኦንግጄቼኦን ወንዝ አፍርሳ ንጹሕ ውኃ የሚፈስበት ውብ መናፈሻ በማድረግ የቱሪስት መዳረሻ አድርገዋለች።
እንግሊዝ በ19ኛው ክፍለ ዘመን በለንደን በብክለቱ ምክንያት "ታላቁ ግማት" ይሰኝ የነበረውን ቴምዝ ወንዝ በጥብቅ ሕጎችና ማጣሪያዎች ወደ ዘመናዊ የቱሪስት ማዕከልነት ቀይረዋለች።
ፈረንሳይ በፓሪስ የሴን ወንዝ ዳርቻዎችን በመኪና መንገድነት ፈንታ ወደ አርቲፊሻል የባሕር ዳርቻነት በመቀየር ለሕዝብ መዝናኛነት አውላለች።
የወንዝ ዳርቻ ልማት ስኬት በአዲስ አበባ ብቻ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን፣ አሁን ላይ የሐይቅ ዳርቻዎችንና የተለያዩ የከተማ መተንፈሻ ስፍራዎችን በማልማት ጠቃሚ የሆኑ ተሞክሮዎች ወደ ሌሎች የሀገራችን ከተሞችም በተግባር እየተሻገረ ይገኛል።
በአጠቃላይ፣ የከተማ ወንዞችን ማልማት የውበት ሥራ ብቻ አይደለም፤ የከተማን ነፍስ የመታደግ፣ የሕዝብን ጤና የመጠበቅና ዘላቂ የኢኮኖሚ መሠረትን የመጣል ስልታዊ ኢንቨስትመንት እንጂ።
ወንዞችን ከብክለት በማዳን አረንጓዴ ሥነ-ምህዳርን ሲመልሱ፣ ይህ ለቀጣዩ ትውልድ የሚተርፍ የነቃ እና ውብ ታላቅ የከተማ ልማት የታሪክ ዐሻራ ነው።
በሰለሞን ገዳ