የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ሂደት ቀጥተኛና ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
በመርሐ ግብሩ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ ማልማት ተችሏል።
በተለይ በዓባይ ተፋሰስ የሚከናወኑ የደን ልማት ሥራዎች መሬቱ ዝናብን አምቆ እንዲይዝ በማድረጋቸው ወደ ግድቡ የሚፈሰው የውሃ መጠን ወጥ እና አስተማማኝ እንዲሆን አስችሏል።
ይህ የተፈጥሮ ሚዛንን የመጠበቅ ሂደት ግድቡ ያለ ምንም የውኃ እጥረት በታቀደለት ጊዜ በሙሉ አቅሙ ውኃ እንዲይዝ ትልቅ አቅም ሆኗል።
ከውኃ ሙሌቱ ባለፈ የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራ ግድቡ ለበርካታ ዓመታት አገልግሎት እንዲሰጥ እና የኃይል ማመንጨት ሂደቱ እንዳይስተጓጎል በማድረግ ረገድ ቁልፍ ሚና ይጫወታል።
በዓባይ ተፋሰስ የተተከሉ ችግኞች የአፈር መሸርሸርን በከፍተኛ ደረጃ ስለሚከላከሉ ወደ ግድቡ የሚገባው የደለል መጠን በእጅጉ ቀንሷል።
ይህም የግድቡን ውኃ የመያዝ አቅም ከመጠበቁም በላይ ኃይል የሚያመነጩ ተርባይኖችን ከብልሽት በመታደግ የኤሌክትሪክ ምርቱ በስኬት እንዲቀጥል እያደረገ ይገኛል።
የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ የአየር ንብረት መጠበቂያ ብቻ ሳይሆን፣ የሕዳሴ ግድብን ኢንቨስትመንት እና የልማት ጉዞ የሚያስቀጥል ታላቅ ብሔራዊ ጋሻ ነው።
የአካባቢ ጥበቃ ሥራው ከግድቡ አሠራር ጋር መቀናጀቱ ዘላቂና አስተማማኝ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምን በተግባር ያሳየ ስኬታማ ሞዴል ሆኖ ይጠቀሳል።
የአረንጓዴ ዐሻራ እና ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ቁርኝት ሀገራችን የልማት አጀንዳዋን በተፈጥሮ ጥበቃ የተደገፈ ለማድረግ ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።
በሃና ምንዳሁን