የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በዩኒቨርሲቲው 76ኛ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ንግግር አድርገዋል።
በንግግራቸውም፣ የሀገራችንን ነባራዊ ሁኔታ እና ታሪካዊ ማነቆዎች የዳሰሰ ጠንካራ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ፕሮፌሰር ብርሃኑ እንዳሉት ኢትዮጵያ ከድህነት ወጥታ ወደ ዕድገት ማማ መሸጋገር የምትችለው በተፈጥሮ ሀብቷ ሳይሆን ጥራት ያለው እና ፍትሐዊ የትምህርት ሥርዓት መገንባት ስትችል ብቻ ነው።
ከደርግ ሥርዓት ጀምሮ ትምህርት ቤቶች እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የፖለቲካ ቁጥጥር እና የርዕዮተ-ዓለም መቅረጫ ማዕከል እንዲሆኑ በመደረጉ፣ የትውልዱ በነፃነት የማሰብ መብት ተነፍጎ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የመሠረታዊ የትምህርት ግብዓቶች አለመሟላት እንዲሁም በቅድመ ልጅነት ትምህርት ደረጃ በመንግሥት እና በግል ትምህርት ቤቶች መካከል ያለው ሰፊ ልዩነት ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር የኢ-እኩልነት ክፍተት መፍጠሩን ተናግረዋል።
የትምህርት ጥራት መጓደል ተፅዕኖው በክፍል ውስጥ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን፣ ለማኅበረሰብ መከፋፈል እና ለተቋማት መዳከም ጭምር ዋነኛ መነሻ መሆኑን ቻንስለሩ አስረድተዋል።
የሰው ኃይል በዕውቀት፣ በክህሎት እና በሥነ-ምግባር ታንጾ አለመውጣቱ ኢትዮጵያዊ አብሮነትን እና ሀገራዊ ስሜትን በማዳከም አደገኛ ግለኝነት እንዲስፋፋ አድርጓል ብለዋል።
ይህ የትውልድ የሞራል ቀውስ በቀጥታ ወደ መንግሥት ተቋማት ዘልቆ በመግባት መሥሪያ ቤቶች ሕዝብን በቅንነት፣ በታማኝነት እና በፍትሐዊነት ከማገልገል ይልቅ በሙስና፣ በአድሏዊ አሠራር እና የተገልጋዩን ማኅበረሰብ ክብር በሚያዋርድ የሞራል ውድቀት እንዲተበተቡ ማድረጉን ፕሮፌሰር ብርሃኑ በንግግራቸው በዝርዝር አንስተዋል።
በለሚ ታደሰ