በኢፌድሬ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የፌዴራል ተቋማት የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ የጋራ መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የአገልግሎቱ ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ፣ ሕዝባችን የመረጃ ፍላጎቱን በአግባቡ እና በወቅቱ እንዲያረካ በየተቋማቱ ያለውን የመረጃ ፍሰት ፍጥነት፣ ጥራት እና ዘመናዊ የዲጂታል ተግባቦት ሥርዓትን በማቀላጠፍ እና በማሳለጥ ረገድ በልዩ የሙያ ብቃት መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ለዘርፉ ስኬት የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ የሥራ መሪዎች እና ባለሙያዎች የላቀ የሥራ አፈጻጸም እና ቁርጠኝነት እንደሚጠበቅ የጠቁሙት ሚኒስትሯ፣ የጋራ መድረኩ በጥናት እና ምርምር በተለዩ ተቋማዊ የመረጃ ተደራሽነት ክፍተቶች ላይ በጥልቀት በመወያየት እና ገንቢ ሐሳቦችን በመለዋወጥ ለቀጣይ ስኬታማ ሥራዎች ታላቅ ስትራቴጂያዊ ግብዓት የሚገኝበት ምቹ አጋጣሚ መሆኑን አመላክተዋል።
ሕዝባችን በሳይንሳዊ መንገድ የሚመራ፣ ወቅቱን የዋጀ፣ እውነተኛነቱ የተረጋገጠ እና ወደፊት የሚያራምደው የተሟላ መረጃ ይፈልጋል ያሉት ሚኒስትሯ፣ ለዚህ ደግሞ መላው የኮሙኒኬሽን ቤተሰብ አገራዊ መረጃዎችን በሚገባ በመተንተን እና በማደራጀት በተፈላጊው ጊዜ እና ፍጥነት ለሕዝብ በማድረስ ረገድ ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።
መረጃ በአሁኑ ዘመን ትልቅ ሀገራዊ እና ተቋማዊ ሀብት መሆኑን በጥብቅ በመገንዘብ፣ ለሕዝብ የሚደርስበትን አግባብ፣ በመረጃ አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች እና ጥንካሬዎችን በየጊዜው እየለዩ እና እየገመገሙ መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
በኢፌዴሪ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስተባባሪነት እና መሪነት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የ2018 በጀት ዓመት የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ሥራዎች አጠቃላይ አፈጻጸም ሪፖርት እንዲሁም በተቋማት የመረጃ ተደራሽነት አተገባበር ተጨባጭ ዳሰሳ ላይ ያተኮረ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቦ ሰፊ ውይይትና የጋራ መግባባት የተደረሰ መሆኑን ከአገልግሎቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።