ጠንካራ ሀገር የምትገነባው በጠንካራ፣ ዘመናዊ እና ገለልተኛ ተቋማት ነው፡፡ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ኢትዮጵያን በሁሉም ዘርፍ ወደ ተሻለ እና አስተማማኝ ምዕራፍ ለማሸጋገር ሰፊ የተቋማት ሪፎርም ተከናውኗል። እነዚህ ሪፎርሞች በኢኮኖሚ፣ በዴሞክራሲ፣ በአገልግሎት አሰጣጥ እና በጸጥታው ዘርፍ ተጨባጭ መዋቅራዊ ለውጦችን እያመጡ ይገኛሉ።
የማክሮ-ኢኮኖሚ እና የፋይናንስ ሽግግር
የኢትዮጵያን ማክሮ-ኢኮኖሚ ለማዘመን የተወሰዱት እርምጃዎች የሀገራችንን የፋይናንስ ሥነ-ምህዳር በአዲስ መልክ እየቀየሩት ይገኛሉ።
በተለይም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዘመናዊ የገንዘብ ፖሊሲን በመተግበር የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰን ማድረጉ ትልቅ ታሪካዊ ስኬት ነው።
ይህ ደፋር እርምጃ በጥቁር ገበያው እና በመደበኛው የምንዛሬ ተመን መካከል የነበረውን ከፍተኛ ልዩነት በማጥበብ ጤናማ የኢኮኖሚ ውድድር እንዲፈጠር በር ከፍቷል።
በተጨማሪም በቅርቡ የተቋቋሙት የኢትዮጵያ ሰኩሪቲ ኤክስቼንጅ (የካፒታል ገበያ) እና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ እና የሀገር ውስጥ ሀብትን በማመንጨት ረገድ የኢኮኖሚያችን አዳዲስ ሞተሮች ሆነዋል።
በሌላ በኩል የፋይናንስ ዘርፉን አማራጭ ለማስፋት በተወሰደው የፖሊሲ እርምጃ የውጭ ባንኮች በሀገራችን የባንክ ዘርፍ ውስጥ እንዲሰማሩ በር ተከፍቷል፡፡
የዲጂታል ፋይናንሲንግ ደግሞ ከመደበኛው ባንክ በላቀ ሁኔታ ለበርካቶች የፋይናንስ ተደራሽነት እየፈጠረ ነው፡፡
ለማሳያም 'ቴሌ ብር' ብቻ ከ58 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን አፍርቶ ከ6.88 ትሪሊዮን ብር በላይ በዲጂታል መንገድ አንቀሳቅሷል፡፡
የዴሞክራሲ፣ የፍትሕ እና የሰላም ተቋማት ግንባታ
የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የለውጡ መንግሥት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ነው። በዚህም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከመንግሥት ተጽዕኖ ሙሉ በሙሉ ነጻ በመሆን በሀገራችን ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ገለልተኛነትን ማረጋገጥ ችሏል።
ይህ ቁርጠኝነቱም በዓለም አቀፍ ደረጃ የ‘A-Status’ ዕውቅናን አጎናጽፎታል። ኮሚሽኑ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የበላይ ጠባቂነት የዜጎችን መብት ያለማንም ጣልቃ ገብነት እየመረመረ ይፋ በማድረግ የዜጎችን ድምጽ በተግባር እያስተጋባ ይገኛል።
ሌላው የለውጡ አንጸባራቂ ትሩፋት የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ነው። ቦርዱ በነጻነት እና በገለልተኝነት በአዲስ መልክ ከተዋቀረ ወዲህ ሁለት ጠቅላላ ምርጫዎችን እና አራት ሕዝበ ውሳኔዎችን በስኬት አከናውኗል፡፡
በቅርቡ በተካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከ54 ሚሊዮን በላይ መራጮችን እና ከ10 ሺህ በላይ እጩ ተወዳዳሪዎችን መዝግቦ በማሳተፍ የሕዝብን አመኔታ መልሶ ማትረፍ ችሏል።
ይህ የተቋማት ግንባታ ለተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ለነጻ ሚዲያ እና ለሲቪል ማኅበራት ሰፊ ምህዳር የፈጠረ የዴሞክራሲያዊ ባህል መሠረት ነው።
ቴክኖሎጂ እና ዘመናዊ የአገልግሎት አሰጣጥ
"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ስትራቴጂን መሠረት በማድረግ አገልግሎት አሰጣጥን ከማንዛዛት እና ከሙስና በማጽዳት ረገድ ቴክኖሎጂ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው።
የመንግሥት የኤሌክትሮኒክ አገልግሎት ፖርታል (e-Services) ዜጎች ከ130 በላይ የመንግሥት አገልግሎቶችን ያለሰው ንክኪ፣ ካሉበት ቦታ ሆነው በኢንተርኔት እንዲያገኙ አስችሏል።
የ'መሶብ' የአንድ ማዕከል አገልግሎት ደግሞ እነዚህን አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል በፍጥነት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡
ይህ አሠራር ደላሎችን እና ቢሮክራሲን በማስቀረት የዜጎችን ጊዜ እና ገንዘብ ታድጓል። ለአገልግሎት ቅልጥፍና እና ለፋይናንስ አካታችነት መሠረት የሆነው የ"ፋይዳ" ብሔራዊ መታወቂያም ከ46 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን በተሳካ ሁኔታ መዝግቧል።
ይህ ሁሉ ሀገራችን እየገነባች ላለው የስማርት ሲቲ (Smart City) እና የዲጂታል ኢኮኖሚ ጠንካራ የጀርባ አጥንት ነው።
የጸጥታው ዘርፍ ጥንካሬ እና ሉዓላዊነት
የዜጎች ደኅንነት እና የሀገር ሉዓላዊነት የየትኛውም ልማት መሠረት በመሆናቸው የፀጥታው ዘርፍ በሪፎርሙ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል።
በዛሬዋ ኢትዮጵያ የደኅንነት እና የፀጥታ አካላት ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ ሆነው የሀገርን ሉዓላዊነት ሌት ተቀን በመጠበቅ ላይ ይገኛሉ።
መከላከያ ሠራዊት፣ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት፣ የፌዴራል ፖሊስ እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር (ኢንሳ) በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች አቅማቸውን አግዝፈዋል።
የፀጥታ ተቋማቱ አሃዳዊ ጥንካሬ እና ቅንጅታዊ አሠራር ኢትዮጵያ የተደቀኑባትን ውስብስብ የውስጥ እና የቀጣናው ፈተናዎች በብቃት እንድታልፍ እና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በማይናወጥ ዐለት ላይ እንድትገነባ አድርጓታል።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ከዚህ የተቋማት ግንባታ እጅግ እያተረፈች ትገኛለች፡፡ ተቋማቱ እየተጠናከሩ በመሄዳቸው ከውስጥም ከውጭም ከተደቀኑባት አደጋዎች አልፋ ወደ ብርሃኑ መንገድ እየወጣች ነው፡፡
ጠንካራ ተቋማትን መገንባት የአንድ ጀንበር ሥራ ባይሆንም፣ የተጀመሩት ተስፋ ሰጪ ለውጦች ሀገራችንን ወደ ተሻለ ከፍታ እንደሚያደርሷት አያጠራጥርም።
ፈተናዎችን ወደ እድል እየቀየረች ያለችው ኢትዮጵያ፣ በጠንካራ ተቋሞቿ ታጅባ የልዕልና ጉዞዋን አጠናክራ ቀጥላለች፡፡
በለሚ ታደሰ