የአውሮፓ ኅብረት በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ባወጣው መግለጫ፤ ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የፕሪቶሪያውን የዘላቂ ግጭት ማቆም ስምምነት እየጣሰ መሆኑን አስታወቀ።
ኅብረቱ እንዳመለከተው፣ ህወሓት ትይዩ የሆነ የክልል ምክር ቤት ለማቋቋም የወሰደው እርምጃ እና የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላን በትግራይ ውስጥ ለማስፈጸም የሚያደርገው እንቅስቃሴ የፕሪቶሪያውን ስምምነት (CoHA) ድንጋጌዎችን በግልጽ የሚጥስ ነው።
በመሆኑም ኅብረቱ በድርጊቱ ላይ ከፍተኛ ስጋት እንዳደረበት አጽንዖት ሰጥቷል።
በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ሰላም እና መረጋጋትን ለማምጣት በአፍሪካ ኅብረት መሪነት የሚደረገውን የአደራዳሪነት ጥረት ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፍ ኅብረቱ አረጋግጧል።