የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ፕላን ቦርድ የከተማዋን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት የሚያሳድግና ግዙፍ ዓለም እና አህጉር አቀፍ ኩነቶችን ለማስተናገድ የሚያስችል አዲስ የአካባቢ ልማት ጥናት /LDP/ ላይ ተወያይቶ ጥናቱን ማፅደቁን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ።

የፀደቀዉ ጥናት ሶስት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች እንዳሉት ከንቲባ አዳነች አመላክተው፤ የትኩረት አቅጣጫዎቹም ፦
1. ኢትዮጵያ በቅርቡ የምታስተናግደው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP-32) ከ80 ሺህ በላይ እንግዶች ወደ መዲናዋ እንደሚያመጣ ይጠበቃል። በአሁኑ ወቅት የከተማዋ ሆቴሎች እና የእንግዳ ማረፊያዎች የመቀበል አቅም 25 ሺህ እንግዶች ብቻ በመሆኑ፣ ይህንን ክፍተት ለመሙላት የተጀመሩ ዘመናዊ የሆቴልና የአፓርትመንት ስታዳርድ አስጠብቆ ማጠናቀቅ እና አዳዲስ ግንባታዎችን በስፋት እንዲከናወኑ ማድረግ ፣
2. የመንገድ ትስስርን ማስፋት እና ማዘመን ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠዉ ሲሆን፣ ይህም የመንገድ ኔትወርኮችን ማስፋፋት፣ ሰፋፊ የእግረኛና የሳይክል መንገዶችን መገንባት እንዲሁም ዘመናዊ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎችንና ተርሚናሎችን ያካትታል።
3. ለታላላቅ ስፖርታዊ ኩነቶች የሚደረግ ዝግጅት፦ ከተማዋ የCOP-32 ጉባኤን የማስተናገድ ዕድል እንዳገኘች ሁሉ፣ የአፍሪካ ዋንጫንም በብቃት ለማስተናገድ እድትችል በዝግጅት ላይ ትገኛለች። በተለይም በአደይ አበባ ስታዲየም ዙሪያ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች የዚሁ ዕቅድ አካል ናቸው ብለዋል።
በአጠቃላይ በCOP እና በFIFA ስታንዳርድ መሠረት የሚከተሉት መሰረተ ልማቶች እንደሚለሙም ከንቲባዋ አስታውቀዋል ፦
• የመንገድ እና የትራንስፖርት መሠረተ ልማት፤
• የሆቴል፣ ሬስቶራንት እና ፔንሲዮን ፣ በርከት ያሉ የተለያዪ የንግድ ቤቶችን ማስፋፋት ልማት፤
• የውኃ፣ የፍሳሽ፣ የቴሌኮም እና የኤሌክትሪክ ኃይል ፣ እና ሌሎች የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት፤
• የወንዝ ዳርቻ ልማት
• ከስታድዮሙ ፊት ለፊት በከፊል እየለማ ባለዉጠ ባለዉ ዊንዶስ ኦፍ አፍሪካ ላይ የአረንጓዴ ፕላዛ፣ የጎልፍ ሜዳ፣ የአዳራሾች፣ የካፍቴሪዎች ፣ የስፓርት ሜዳዎች ፣ የተለያዪ መዝናኛዎች እና መሰል ልማቶች ይሰራሉ።
የአሰራር ሂደቱ አዳዲስና ነባርና አዳዲስ መሠረተ ልማቶችን አስተሳስሮ በስታዲየሙ ዙሪያ ነባር መሰረተ ልማቶችን ባሉበት ማደስን ቅድያ በመስጠት፣አዳዲሶቹን ደግሞ በነዋሪው፣ በመንግሥት፣ በባለሀብቱ እና በተቋማት ቅንጅት የሚለማ ይሆናል ብለዋል።
የትግበራ ሂደቱም ነዋሪዉን በስፋት በማወያየት በፀደቀዉ ፕላን መሰረት ነዋሪዉን እያገዝን ራሱ እንዲያለማዉ ማድረግ ቅድሚያና ትኩረት ይሰጠዋል ሲሉ ገልጸዋል።
ይህ እድል ለከተማችን ነዋሪዎች ሰፊ የስራ እድል እና የኢኮኖሚ መነቃቃት የሚፈጥር በመሆኑ ተባብረን በጋራ እንድናሳካው ጥሪ አቀርባለሁ ብለዋል።