የለውጥ ወይም የሪፎርም ጉዞ ምንጊዜም አልጋ በአልጋ ሆኖ አያውቅም። በዓለም ታሪክ በግልጽ እንደምንገነዘበው፣ የሪፎርም ማዕበልን የተቀላቀሉ በርካታ ሀገራት፣ በጠንካራ፣ ጥልቀት ያለው እና ራዕይ ሰነቅ አመራር ካልተመሩ ከስኬት ይልቅ ወደ ከፋ ማጥ ውስጥ ይዘፈቃሉ።
የለውጥ ሒደቶች የነባሩን መፍረስ እና አዲሱን መገንባት የሚያስተናግዱ በመሆናቸው፣ በሽግግሩ ወቅት የሚፈጠረውን ክፍተት እና ውዥንብር መሻገር የሚቻለው የማይናወጥ የመሪነት ጽናት ሲኖር ነው።
ያለ ጠንካራ የተቋማት ግንባታ እና ቆራጥ አመራር፣ ማሻሻያዎች በቀላሉ ተቀልብሰው ሀገራትን ወደ ለየለት ትርምስ ይከትታሉ። የለውጥን ሸራ ገልጦ፣ ማዕበሉን አቋርጦ የብልጽግና ወደብ መድረስ የሚቻለው ብርቱ የመሪነት ጥበብ፣ ትዕግሥት እና ስልታዊ ብልሃት ሲዋሐዱ ብቻ ነው።
የኢትዮጵያችን የሪፎርም ጉዞ የእሳቤ አውድ እና መነሻም ይኸው ሐቅ ነው። ሀገራችን ከነበረችበት ፖለቲካዊ ስብራት፣ ኢኮኖሚያዊ ድቀት እና ማኅበራዊ ማነቆዎች ተላቅቃ፣ ሁለንተናዊ ብልጽግናዋን ለማረጋገጥ መነሻዋ ያደረገችው የመደመር እሳቤን ነው።
ይህ ጥልቅ ሀገር በቀል እሳቤ የትናንት የታሪክ ጠባሳዎችን እያከመ፣ የዛሬን ጸጋዎች አጉልቶ እና አቀናጅቶ፣ የነገውን ብሩህ ተስፋ ለመገንባት የሚያስችል የጽናት መሠረት ሆኖ አገልግሏል። የለውጥ ጉዟችን ከመፍረስ ወደ መገንባት፣ ከመለያየት ወደ መተባበር የተደረገ ታሪካዊ ሽግግር ነው።
በፖለቲካው መስክ የሕዝብን የዴሞክራሲ ጥማት ለማርካት እና የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት የተሠሩት ሥራዎች መዋቅራዊ መሠረት ያላቸው ናቸው። የሐሳብ ብዝኃነትን በማስተናገድ፣ የዜጎችን እኩልነት እና አብሮነት የሚያጠናክሩ እርምጃዎች ተወስደዋል።

በተለይም የጸጥታ እና የፍትሕ አካላትን ከፖለቲካ ወገንተኝነት በማላቀቅ የሕዝብ መከታ እና የሀገር ደጀን እንዲሆኑ የተደረገው የተቋማት ግንባታ ሪፎርም የጠንካራ አመራር ፍሬ ነው። ይህ የለውጥ ሒደት ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር እና የዴሞክራሲ ባህልን ለማጽናት ትልቅ አቅም ፈጥሯል።
በኢኮኖሚው መስክ የተመዘገቡት አስደናቂ ስኬቶች የለውጡን ፍሬያማነት እና የአመራሩን ብቃት ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ። ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የኢትዮጵያን አንጡራ ሀብቶች እና እምቅ አቅሞች በሚገባ ሥራ ላይ በማዋል፣ ከግብርና እስከ ማዕድን፣ ከቱሪዝም እስከ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ዘርፎች ጉልህ መነቃቃትን ፈጥሯል።
የከተሞቻችንን ገጽታ ከመሠረቱ የሚቀይሩ የኮሪደር ልማቶች፣ ግዙፍ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ እና አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል የተወሰዱ ደፋር እርምጃዎች ናቸው።
በግብርናው ዘርፍ፣ በተለይም በስንዴ ልማት እና በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሮች የተገኙት ድሎች የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አልፈው ለዓለም ምሳሌ የሚሆኑ ትሩፋቶች ናቸው። በማኅበራዊው ዘርፍም የትውልድን አቅም የሚገነቡ፣ የትምህርት ጥራትን የሚያሳድጉ እና የዜጎችን የኑሮ ጫና የሚያቀልሉ አያሌ ተግባራት ተከናውነዋል፤ ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችም በሕዝብ ንቁ ተሳትፎ እና በቆራጥ አመራር ክትትል ወደ ፍጻሜ እየገፉ ይገኛሉ።

የውጭ ጉዳይ እና የዲፕሎማሲ ስኬቶቻችን የሪፎርሙ ሌላኛው ደማቅ የድል አክሊል ናቸው። ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን፣ ሉዓላዊነቷን እና ክብሯን በሚያስከብር ገቢር ነበብ መርሕ ላይ ተመሥርታ፣ ከጎረቤት ሀገራት እስከ ዓለም አቀፍ መድረኮች ያላትን ተጽዕኖ ፈጣሪነት አሳድጋለች።
የሀገራችንን የጂኦ-ፖለቲካዊ እና ጂኦ-ስትራቴጂያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፣ ሰላም እና ትብብርን ማዕከል አድርጎ የሚመራው ውጫዊ ግንኙነታችን፣ ጠንካራ እና አርቆ አሳቢ አመራር ያመጣው የላቀ ውጤት ነው። ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላት ተሰሚነት እና ተቀባይነት በአዲስ መልክ ታድሷል።

በአጠቃላይ፣ የሪፎርሙ ሒደት ዘርፈ ብዙ እና ውስብስብ ፈተናዎች ቢበዙበትም፣ ጠንካራው፣ አስተዋዩ እና ራእይ ሰነቁ አመራር ከሕዝቡ ጽናት ጋር ተዳምሮ ሀገራችንን ከማዕበሉ አሻግሯታል።
በአጭር ጊዜ ውስጥ በየዘርፉ የታዩት እነዚህ ተጨባጭ ድሎች፣ ኢትዮጵያ በጀመረችው የብልጽግና ጎዳና ወደ ኋላ እንደማትመለስ እና የታለመላትን የላቀ ከፍታ በእርግጠኝነት እንደምትጎናጸፍ የሚያረጋግጡ ሕያው ምስክሮች ናቸው።
ሀገራችን በልጆቿ የጋራ አንድነት፣ በጠንካራ እና ቆራጥ መሪነት ተጋምዳ የገጠሟትን ተግዳሮቶች ሁሉ በማለፍ ብሩህ የወደፊት ዕጣ ፈንታዋን በተግባር ታረጋግጣለች። በእርግጥም፣ ጊዜው ፈታኝ ቢሆንም፣ ጠንካራው ሪፎርም ኢትዮጵያ ታሳካለች የሚለውን ቃል አጽንቷል።
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ