በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር መሐመድ አልሃሜሊ፣ ኢትዮጵያ በቅርቡ ያካሄደችውን 7ኛ ብሔራዊ አጠቃላይ ምርጫ ስኬታማነት አስመልክቶ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዳይሬክተሩ ይህንን የገለጹት፣ በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የኢፌዴሪ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ዶ/ር ጀማል በከር ጋር በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች እና የሁለትዮሽ ግንኙነትን ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ ባካሄዱት ውይይት ላይ ነው።
በውይይቱ ወቅት አምባሳደር ዶ/ር ጀማል በዋና ዋና አገራዊ አጀንዳዎች ዙሪያ ለዳይሬክተሩ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
እ.ኤ.አ. ሰኔ 1 ቀን 2026 ዓ.ም የተካሄደውን እና በአፍሪካ ኅብረትና በኢጋድ (IGAD) ታዛቢ ልዑካን ሰላማዊ እና ተዓማኒ መሆኑ የተረጋገጠውን 7ኛውን ብሔራዊ አጠቃላይ ምርጫ በዝርዝር አቅርበዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉን የአየር ንብረት ጉባኤ (COP32) በሊቀመንበርነት ለማስተናገድ እያደረገች ያለውን ዝግጅት አብራርተዋል።
በትግራይ ክልል ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ማብራሪያ የሰጡት አምባሳደሩ፣ ህወሓት የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በመጣስ የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር በሕገ-ወጥ መንገድ ማፍረሳቸውን አስታውቀዋል።
አምባሳደሩ አክለውም፣ የፌዴራል መንግሥቱ የተፈጠረውን ሁኔታ ለማረጋጋት እና ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
ገለጻውን ተከትሎ መሐመድ አልሃሜሊ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ኢትዮጵያ ስኬታማ እና ሰላማዊ ብሔራዊ ምርጫ በማካሄዷ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
አክለውም ኢትዮጵያ የኮፕ32 የአየር ንብረት ጉባኤን ለማዘጋጀት መመረጧን አድንቀው፣ ይህ ታላቅ ዓለም አቀፍ መድረክ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው አፍሪካ ኩራት እና ትልቅ አቅም መሆኑን ገልጸዋል።
የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እና በጋራ ለመሥራት ያላትን ሙሉ ዝግጁነት አረጋግጠዋል።
ሁለቱ ወገኖች በኢትዮጵያ እና በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች መካከል ያለውን ጠንካራ እና ስትራቴጂካዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ዘርፎች ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ መምከራቸውን በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።