የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የነበረው የታዛቢነት ተሳትፎ ኢትዮጵያ በራሷ አቅም ምርጫዋን መታዘብ እንደምትችል ያሳየ መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ እውነቱ አለነ ገለጹ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 27ኛ መደበኛ ስብሰባ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የ2018 በጀት ዓመት የ11 ወራት አፈፃፀምን ገምግሟል።
የቋሚ ኮሚቴው ዋና ሰብሳቢ እውነቱ አለነ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በተቋማዊ ለውጥ በዲጂታል አቅም ግንባታ እና በዓለም አቀፍ እውቅና ያስመዘገበው ውጤት ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን የሚያሟላ ጠንካራ ተቋም መሆኑን ያረጋግጣል።
ኮሚሽኑ በፖሊስ ጣቢያዎች እና በማረሚያ ቤቶች የሚያደርገው ክትትል የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰው፣ በግጭት ዐውድ ውስጥ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ የሚወጡ ሪፖርቶች ታማኝነታቸውን በሚገባ ማረጋገጥ እና በጥንቃቄ መከወን እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን በተመለከተ የሚከታተላቸው ራሱን የቻለ ተቋም እንዲኖር የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ኮሚሽኑ ባለፉት 11 ወራት በፖለቲካዊ፣ በማኅበራዊ እና በኢኮኖሚያዊ መብቶች ዙሪያ የክትትልና የምልከታ ሥራዎችን በስፋት መሥራቱም ተመላክቷል።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ተቋሙ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የክትትል ቡድን በማሰማራት ምርጫው በስኬት መጠናቀቁን ማረጋገጡን ተናግረዋል።
በፖሊስ ጣቢያዎች፣ በማረሚያ ቤቶች እና በማቆያ ስፍራዎች የታራሚዎች አና የተጠርጣሪዎች አያያዝ ላይ መሻሻሎች ቢታዩም፣ ተጨማሪ ሥራዎች እንዳሉ ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል ፍልሰተኞች እና ስደተኞች የተሻለ የሕግ ጥበቃ እንዲያገኙ አሳሪ ህጎች መውጣት እንዳለባቸው እንዲሁም ለሰብአዊ መብት ጥሰት መንስኤ የሚሆኑ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ ሊፈቱ እንደሚገባ ኮሚሽኑ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በተቋማዊ ለውጥ ጠንካራ ዕድገት ማስመዝገቡ የተገለጸ ሲሆን፣ ተቋሙ በዓለም አቀፍ ደረጃ “A Status” ማግኘቱና በአፍሪካ የብሔራዊ ሰብአዊ መብት ተቋማት ኔትወርክ የምክትል ሰብሳቢ ኃላፊነት መያዙ የዚህ ስኬት ማሳያ መሆኑ ተጠቁሟል።
በተለይም በዲጂታል ዘመን የሚስፋፉ ሀሰተኛ መረጃዎች ለሰብአዊ መብቶች ሊያስከትሉ የሚችሉትን አደጋ ለመቀነስ ኮሚሽኑ የዲጂታል አቅሙን ማጠናከሩም ከዋና ዋና ስኬቶቹ አንዱ ሆኖ ተጠቅሷል።
በመስከረም ቸርነት