ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነጻ፣ ፍትሃዊ እና ተዓማኒ ሆኖ መጠናቀቁ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን አሸናፊነት ያረጋገጠ መሆኑን የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ኅብረት (ኢዴኅ) ገለጸ።
የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ኅብረት (ኢዴኅ) እንደገለጸው፤ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሙሉ በሙሉ ሰላማዊ፣ ነጻ፣ ፍትሃዊ እና ተዓማኒ ሆኖ መጠናቀቁ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን አሸናፊነት ያረጋገጠ ነው።
አብላጫ ድምጽ ያገኘው ብልፅግና ፓርቲ የተጣለበትን ታላቅ ሕዝባዊ አደራ በመቀበል፣ የመረጠውንም ሆነ ያልመረጠውን ሕዝብ በእኩል በቅንነት እና በታማኝነት ማገልገል ይጠበቅበታል ብሏል።
በምርጫውን ላሸነፈው ብልፅግና ፓርቲም የእንኳን ደስያለህ መልዕክት በማቅረብ መልካም የሥራ ዘመን ተመኝቷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሂደቱን በገለልተኝነት፣ በብቃትና በትዕግስት በመምራት የሕዝብ አገልጋይነቱን በተግባር ማሳየቱን ገልጿል።
ምርጫው ሰላማዊ እና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን ሌት ተቀን በመሥራት ኃላፊነቱን በብቃት መወጣቱንም ጠቁሟል።
ሀገራችን ካጋጠሟት በርካታ ተግዳሮቶች አኳያ እጅግ ውስብስብ የሆኑ ሀገራዊ ሂደቶችን በከፍተኛ ሙያዊ ብቃት፣ ገለልተኝነት እና ግልጽነት በመምራት ረገድ የምርጫ ቦርድ ሚና የሚደነቅ መሆኑን አመልክቷል።
ቦርዱ ያጋጠሙትን ችግሮች በግልጽ ለሕዝብ ይፋ በማድረግ፣ የሕዝብን ድምጽ ለመጠበቅ እና ሰላማዊ የዲሞክራሲ ምህዳር ለመፍጠር ያደረገው ጥረት ታሪክ የማይዘነጋው አኩሪ ተግባር በመሆኑ ከፍተኛ አድናቆቱን መግለጹን ኢዜአ ዘግቧል።