የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ኢትዮጵያ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የተካሄደውን 7ኛ ጠቅላላ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ በማጠናቀቋ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፈ።
የኢጋድ ሴክሬተሪያት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 14 ቀን 2018 ዓ.ም ይፋ ባደረገው ውጤት መሠረት፣ በአብላጫ ድምፅ አሸናፊ ለሆኑት ብልጽግና ፓርቲ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፏል።
ተቋሙ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ሂደቱን በታማኝነት እና በከፍተኛ ሙያዊ ብቃት በመምራት ረገድ ላሳየው ቁርጠኝነት አድናቆቱን ገልጿል።
ለምርጫው በሰላማዊ እና በሥርዓት መጠናቀቅ ቀዳሚውን ሚና ለተጫወቱት የኢትዮጵያ ሕዝቦችም ዕውቅና ሰጥቷል።
የምርጫው በተሳካ ሁኔታ መከናወን ኢትዮጵያ ለዴሞክራሲያዊ አስተዳደር እና ለሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ያላትን ቀጣይነት ያለው ቁርጠኝነት የሚያንጸባርቅ መሆኑን በመግለጫው ተጠቅሷል።
ኢጋድ ኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር፣ አካታች ውይይትን ለማሳደግ እንዲሁም ሰላም፣ መረጋጋት እና ዘላቂ ልማትን ለማስቀጠል ለምታደርገው ጥረት ያለውን ጽኑ እምነት ገልጿል።
በመጨረሻም ኢጋድ በቀጣናዊ ትብብር፣ ውህደት፣ ሰላም፣ መረጋጋት እና ዘላቂ ልማት ዙሪያ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ይበልጥ በቅርበት ለመሥራት ያለውን ዝግጁነት በድጋሚ አረጋግጧል።