በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የዜጎችን የዕለት ተዕለት ሕይወት በከፍተኛ ደረጃ እየለወጠ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያብራሩት "ኢትዮጵያ ታከናውናለች" በሚል መሪ ቃል በተካሄደው መድረክ ላይ የዲጂታል ኢትዮጵያ አካል የሆነው የዲጂታል መታወቂያው እያመጣ ያለውን ለውጥ በአብነት በማንሳት ነው፡፡
ከዚህ ቀደም ከመደበኛው የፋይናንስ ሥርዓት ውጭ የነበሩ፣ የባንክ አካውንትም ሆነ የንግድ ምዝገባ ያልነበራቸው ዜጎች በ'ፋይዳ' ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት ውስጥ በመታቀፋቸው ብቻ ሕይወታቸው እየተቀየረ መምጣቱን አስረድተዋል።

ዜጎች የዲጂታል ክፍያ ሥርዓትን መጠቀም መጀመራቸው የፋይናንስ ታሪክ እና መተማመንን እንደፈጠረላቸው አንስተዋል፡፡
ይህ መተማመንም ለተሻለ የፋይናንስ ተጠቃሚነት በር እንደከፈተላቸው እና በሕይታቸው ላይ ለውጥ እያመጣ መሆኑን አውስተዋል።
በዚህም ምክንያት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከዚህ ቀደም ሊያገኟቸው የማይችሉትን ዕድሎች አሁን ማግኘት መቻላቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡
የትራንስፎርሜሽኑ ዋነኛ መለኪያም እኚህ የምንገነባቸው ተቋማት እና የምናሻሽላቸው የዜጎች ሕይወት መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
ይህ የምጣኔ ሀብት ማሻሻያውን ከዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጋር አስተሳስሮ የመምራት አቅም የእውነተኛው "መደመር" መንፈስ ውጤት መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለው ገልጸዋል።
በለሚ ታደሰ