ኢትዮጵያ ከድኅነት አዙሪት ወጥታ ወደ ብልፅግና ማማ ለመሸጋገር የምታደርገው ጉዞ በጠንካራ የኢኮኖሚ ሪፎርም ታጅቦ አስደናቂ ስኬቶችን እያስመዘገበ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ባደረጉት ንግግር እንዳበሰሩት፣ ኢትዮጵያ በዚህ የበጀት ዓመት 10 ነጥብ 2 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት እንደምታስመዘግብ ይጠበቃል። ይህ አሃዝ በአፍሪካ አኅጉር ፈጣኑ ዕድገት ሲሆን፣ ሀገራችን የጀመረችው ሪፎርም ትክክለኛ ፍሬ እያፈራ መሆኑን ያረጋግጣል። እነዚህ ስኬቶች በአጋጣሚ የመጡ ሳይሆኑ፣ መንግሥት "መፍጠር፣ መፍጠንና መዝለልን" እንደ ዋና የልማት ስልቶች በመውሰዱና በወሰናቸው ከባባድ ውሳኔዎች የተገኙ ናቸው።
መንግሥት ለኢኮኖሚ ችግሮች የሚሰጠው መፍትሔ በርዕዮተ ዓለም የታጠረ ሳይሆን፣ በተግባር በሚታይ ውጤት ላይ የተመሠረተ "ገቢር ነበብ" (Pragmatic) የኢኮኖሚ ፍልስፍና ነው።
ከለውጡ በፊት ኢኮኖሚው በከፍተኛ ዕዳ ተሸብቦ እና በማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ተፈትኖ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ይህን የውድቀት ታሪክ መቀየር ተችሏል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳስታወሱት፣ ከ30 በመቶ በላይ ደርሶ የነበረው የዋጋ ግሽበት በከፍተኛ ሁኔታ በማሽቆልቆል፣ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ወደ ነጠላ አሃዝ መውረድ ችሏል።
ይህንንም ውጤት ለማሳካት ጥብቅና ዘመናዊ የገንዘብ ፖሊሲ ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን፣ መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ ቀጥታ የሚወስደው ብድር ሙሉ በሙሉ እንዲቆም ተደርጓል።ኢኮኖሚያችን ከዕዳ ወደ ምንዳ እንዲሸጋገር በማድረግ፣ ለትውልድ ምንዳ እንጂ ዕዳ አናወርስም በሚል መርህ የሀገራችንን የዕዳ ጫና በከፍተኛ ሁኔታ ማቃለል ተችሏል።
በሌላ በኩል የሀገሪቱ የወጪ ንግድ ወደ ታሪካዊ ከፍታ እያመራ ይገኛል። ከሸቀጦች ወጪ ንግድ በ2013 በጀት ዓመት 3 ነጥብ 62 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ይገኝ የነበረው ገቢ፣ በተወሰዱት የተሟሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች በ2017 በጀት ዓመት 8 ነጥብ 3 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ማግኘት ተችሏል።
በተጨማሪም የግሉን ዘርፍ የኢኮኖሚው ሞተር ለማድረግ በተወሰዱ ደፋር እርምጃዎች ለግል እና ለውጭ ኢንቨስትመንት ዝግ የነበሩ እንደ ቴሌኮሙኒኬሽን፣ የባንክ ዘርፍ እና የካፒታል ገበያ ለውድድር ክፍት ሆነዋል።
የሀገር ውስጥ የልማት ፋይናንስን በራስ አቅም ለመሸፈን በተደረገው ርብርብ፣ በ2013 በጀት ዓመት 315 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የነበረው ጠቅላላ የመንግሥት ገቢ በ2017 በጀት ዓመት ወደ 90 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ከፍ ብሏል።
መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግርን ለማረጋገጥ በተሰሩ ሥራዎች፣ የግብርናው ዘርፍ በ2013 በጀት ዓመት ያመርት ከነበረው 356 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ዋና ዋና የሰብል ምርት፣ በ2017 በጀት ዓመት ወደ 836 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ማደግ መቻሉ የሪፎርሙን ጥልቀት ያሳያል።
ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የሥራ አጥነትን ችግር ለመቅረፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገ ሲሆን፣ ባለፉት አራት ዓመታት ብቻ ለ15 ሚሊዮን ዜጎች በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል።
ፋይናንስን አካታች ከማድረግ አንጻርም ለግሉ ዘርፍ የተሰጠው የብድር ድርሻ በ2010 ከነበረበት 56 ነጥብ 3 በመቶ በ2017 ወደ 77 በመቶ ከፍ ማለቱ ሪፎርሙ አምራቹን ማኅበረሰብ እንዴት እያበረታታ እንደሚገኝ ያረጋግጣል።
በአጠቃላይ፣ የመደመር እሳቤን መሠረት አድርጎ ተግባራዊ የተደረገው የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ሪፎርም ሀገራችንን ከድኅነት አዙሪት በማውጣት ላይ ይገኛል። ኢትዮጵያ ውስብስብ ፈተናዎቿን ተቋቁማ፣ በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ፣ በእርግጥም "ታከናውናለች!" የሚለውን እውነት ለዓለም በተግባር አሳይታለች።
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ