በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኘው የኦሞ ወንዝ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ምሰሶ ከመሆኑ ባለፈ ለኢትዮጵያ አዲስ የቱሪዝም ፋና ወጊ እየሆነ ነው፡፡
ይህ ድንቅ ስፍራ ከጠምባሮ ልዩ ወረዳ መቀመጫ ሙዱላ ከተማ በ42 ኪ.ሜትር፣ እንዲሁም ከአዲስ አበባ በ366 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።
ሰው ሰራሽ ጥበብ ከተፈጥሮ ውበት ጋር የተዋሀዱበት ይህ ስፍራ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር ጎብኚዎች በስፋት ይጎበኛል።
በታላቁ የግልገል ግቤ 3 የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት አማካኝነት የተፈጠረው ግዙፍ ሐይቅ ለማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያና ለኦሮሚያ ክልሎች እንደ ማገናኛ ድልድይ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
ሐይቁ የጉማሬዎች፣ ግዙፍ አዞዎችና የበርካታ የዓሳ ዝርያዎች በውስጡ ይገኛሉ የሐይቁ ዳርቻዎች ደግሞ በአስደናቂና ብርቅዬ አዕዋፋት ዝማሬ የታጀቡ ናቸው።
አካባቢው በአስደናቂ ዋሻዎች፣ በረድፍ በሚፈሱ ፏፏቴዎች፣ በወርቃማ ቀለም ባሸበረቁ አለቶችና በጥቅጥቅ ደኖች የተከበበ በመሆኑ ለተፈጥሮ አፍቃሪዎች ተመራጭ መዳረሻ ሆኗል።
የኦሊዶ (ዞጎ) ጠበል ለመዝናኛ ብቻ ሳይሆን ለባህላዊ ሕክምና አገልግሎት የሚውለው ይህ ጠበል፣ የወንዙ ሌላኛው ድብቅ ስጦታ ነው።
ስፍራው እንደ ሀላላ ኬላ ሪዞርት፣ ጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ እና ኮይሻ ካሉ ታዋቂ የቱሪስት መዳረሻዎች ጋር በቅርብ ርቀት የሚገኝ በመሆኑ የቱሪዝም ትስስሩን ጠንካራ ያደርገዋል።
በቢታንያ ሲሳይ