Search

የችግኝ ተከላው የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ያስቻለን ሀገራዊ ስኬት ነው፦ አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

ዓርብ ሰኔ 19, 2018 64

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት "ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ቃል ያዘጋጀውን የአረንጓዴ ዓሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ዛሬ ማለዳ ላይ አከናውኗል።

በችግኝ ተከላው  የተሳተፉት የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ በዓለም አቀፍ ደረጃ አርዓያ መሆን የቻለችበትን ታላቅ ስኬት አብራርተዋል።

"ይህ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የሀገራችንን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ፣ የአፈር መሸርሸርን ለመከላከልና የከርሰ ምድር ውሃን ለማበልጸግ የተጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው" ያሉት አፈ ጉባኤው፣ ኢትዮጵያ በዘርፉ ያገኘቻቸውን ዘርፈ-ብዙ ኢኮኖሚያዊና ተፈጥሯዊ ጥቅሞች በዝርዝር አስገንዝበዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (/) በበኩላቸው፣ የአረንጓዴ ዓሻራ ንቅናቄ ለትውልድ የሚተርፍ ዘላቂ ሀብት መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ ንቅናቄ የተገኘው ትልቁ ስኬት የአየር ንብረት ለውጥን በጽናት መቋቋም መቻሉና ማኅበረሰባችንን በተለይም ወጣቱን ክፍል  ለልማት ማሰለፍ ችልሏ ብለዋል፡፡

የዘንድሮው መሪ ቃል "ተስፋን እንትከል" እንደሚለው ሁሉ፣ እያንዳንዱ ዛሬ የሚተከል ችግኝ ለሀገራዊ ብልጽግና ትልቅ ተስፋ የሚሰንቅ መሆኑን የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይህንን ሀገራዊ ንቅናቄ በፖሊሲና በበጀት ከመደገፍ ባለፈ፣ አባላቱ በየምርጫ ክልሎቻቸው በመውረድ ሕዝቡን በማስተባበርና የተተከሉ ችግኞችን ክትትል በማድረግ ረገድ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ አስታውቀዋል፡፡

በሕይወት አበበ