ተፈጥሮ ሲቆጣ ያጠፋል፤ ሲታከም ግን ሕይወትን መልሶ ያለመልማል። ይህ እውነታ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሀላባ ዞን ዌራ ዲጆ ወረዳ ለምትገኘው ሲንቢጣ ቀበሌ ህያው ምስክር ነው።
ለዘመናት በተፈጥሮ አደጋ እና በተረጂነት ስትፈተን የቆየችው ሲንቢጣ፣ ዛሬ ላይ የገጠር ትራንስፎርሜሽን እና የአምራችነት ህያው ሞዴል ሆና መገኘቷ ብዙ የሚያስተምረን ትልቅ ታሪክ አላት።
አብላጫው መልክዓ ምድሩ ሜዳማና አቀማመጡም በስምጥ ሸለቆ ውስጥ በመሆኑ የሀላባ ዞን ለዘመናት ለከፍተኛ የጎርፍ መጥለቅለቅ እና ለአፈር መሸርሸር ሲጋለጥ ቆይቷል።
በተለይም የሲንቢጣ ቀበሌ አርሶ አደሮች ክረምት በመጣ ቁጥር በጎርፍ ስጋት፣ በበጋ ደግሞ በከፍተኛ የውኃ እጥረት እርሻቸው ሲበላሽና እንስሶቻቸው ሲጎዱባቸው ማየት የዘወትር ዕጣ ፈንታቸው ነበር።
ይህ ተደጋጋሚ የተፈጥሮ አደጋ ማኅበረሰቡን ለተረጂነት ከማጋለጡም በላይ፣ ከዚህ አዙሪት መውጣት አይቻልም ወደሚል የተስፋ መቁረጥ ሥነ-ልቦና ገፍትሮት ቆይቷል።
ነገር ግን ያ የጨለማ ታሪክ ተቀየረ። በሲንቢጣ የተመዘገበው የመጀመሪያው ትልቅ ድል ተፈጥሮን መዋጋት ትቶ በተግባር ማከም መጀመር ነበር።
በዚህም አደጋ ይዞ የሚመጣውን የጎርፍ ውሃ በአግባቡ በመጠለልና አቅጣጫውን በማስቀየር የከርሰ ምድር ውሃ እንዲሞላና እንዲያገግም ተደረገ።
በአካባቢው በተሰራው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት አፈሩ መልሶ በመለመለሙና እርጥበት አዘል በመሆኑ፣ ዛሬ አርሶ አደሮች የከርሰ ምድር ውኃን በመጠቀም በዓመት ከአንድ ጊዜ በላይ በጥራት ማምረት ችለዋል። በዚህም ትናንት ስጋት የነበረው ጎርፍ ዛሬ ወደ ትልቅ ፀጋነት ተቀይሯል።
ከዚህ አካላዊ የልማት ስራ በላይ ደግሞ አስደናቂው እና ትልቁ ስኬት የአስተሳሰብ ለውጥ መምጣቱ ነው። ነዋሪው የዝናብ መምጣትን ብቻ ከመጠበቅ ሰንሰለት ወጥቶ፣ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የራሱን ዕድል በራሱ መወሰን እንደሚችል በተግባር አሳይቷል።
በአሁኑ ወቅት ከ2 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በከርሰ ምድር ውኃ እየለማ የሚገኝ ሲሆን፣ ቀድሞ በአንድ ዓይነት ሰብል ብቻ ይተዳደር የነበረው ማኅበረሰብ አሁን ላይ የምርጥ ዘር በቆሎ ብዜትን ጨምሮ ከፍተኛ የገበያ ተፈላጊነት ያላቸውን አትክልትና ፍራፍሬዎች በስፋት እያመረተ ለገበያ ማቅረብ ጀምሯል።
ይህ ስኬት ኢትዮጵያ ከያዘችው በምግብ ራስን የመቻል ታላቅ ግብ ጋር በቀጥታ የተሳሰረ ሲሆን፣ በሌላ በኩል አረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ከመትከል ባለፈ የሕይወት ዘይቤን ሙሉ በሙሉ የመቀየር የህልውና ጉዳይ መሆኑን በሲንቢጣ በተጨባጭ የታየበት ማረጋገጫ ነው።
የጎርፍ መጥለቅለቅ እና የድርቅ አደጋ ተጋላጭነት ታሪክ ዛሬ ላይ ሙሉ በሙሉ በመስኖ እና በአምራችነት ተተክቷል። የተሠራው ተፈጥሮን የማከም ድንቅ ተግባር አፈሩን ብቻ ሳይሆን፣ የተረጂነት ሥነ-ልቦናን ጭምር በማከም የአርሶ አደሮቹን ተስፋ ያለመለመ ሆኗል።
ሲንቢጣ ዛሬ ላይ የኢትዮጵያን የገጠር ትራንስፎርሜሽን ራዕይ መሬት ላይ በተግባር በማውረድ፣ ለሌሎች የሀገራችን ክፍሎች ታላቅ የልምድ መቅሰሚያ ማዕከል ለመሆን በቅታለች።
በሲሳይ ደበበ