ኢትዮጵያ በታሪኳ ማዕበላትና ፈታኝ ውጣ ውረዶች ውስጥ ስትጓዝ፣ ለአፍታም ቢሆን ከልቧ ያልጠፋ እና ከትውልድ ትውልድ በደም ሲያስተላልፍ የኖረ አንድ ታላቅ የህልውና፣ የልማት እና የክብር ጥያቄ አለ እሱም የባሕር በር ጉዳይ ነው!
ዛሬ ላይ እያንዳንዱ ኩሩ ኢትዮጵያዊ፣ እያንዳንዱ ንቁ ወጣት፣ ምሁር እና ከዳር እስከ ዳር ያለው አገር ወዳድ በሙሉ ዓይኖቹን ከዚህ ሰማያዊ ብሔራዊ አጀንዳ ላይ ፈጽሞ አይነቅልም።
ይህ ጉዳይ ጊዜያዊ የፖለቲካ ፍጆታ ወይም የቅንጦት ወሬ ሳይሆን፣ የሀገራዊ ሉዓላዊነታችን ዋነኛ ምሰሶ፣ የኢኮኖሚ ነፃነታችን ፅኑ ማረጋገጫ እና በቀጠናው ላይ የነበረንን ታሪካዊ የንግሥና፣ የልዕልና እና የበላይነት ክብር ዳግም የመመለስ ታላቅ የትውልድ ታሪካዊ አደራ ነው።
በየዕለቱ በሚዲያና በተለያዩ የዲጂታል መድረኮች ላይ የሚፈበረኩ፣ የህዝባችንን ትኩረት ለመስረቅ የሚወረወሩልን ትናንሽና ጊዜያዊ አጀንዳዎች ሁሉ ከዚህ ታላቅ ሀገራዊ ጥቅም እና ስልታዊ ብሔራዊ እሴት በታች ናቸው። ትልቁና ዋነኛው የኢትዮጵያ አጀንዳ የባህር ላይ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥና የሀገሪቱን ዘላቂ ጥቅሞች በፅናት ማስከበር ነው።
ለዚህ ነው ህዝባችን በየቀኑ ከሚከሰቱ ሰው ሰራሽ ውዝግቦችና አቅጣጫ አስላሽ ወሬዎች በላይ አሻግሮ በማየት፣ ስልታዊ በሆነ ፅናት በትልቁ ምስል ላይ ብቻ ትኩረቱን ያደረገው።
እኛን ከተፈጥሯዊና ታሪካዊ መብታችን ለማራቅ የሚደረጉ ስነልቦናዊ ጦርነቶችና የክስተቶች ድግሶች የነቃውን የኢትዮጵያ ህዝብ ልብ ሊገዙ ወይም አቅጣጫ ሊያስቱት አይችሉም።
ታሪክን ወደኋላ መለስ ብለን በጥልቀት ስንመረምር፣ ኢትዮጵያን ያለ ባሕር በር እንድትቀር በረቀቀ የጂኦፖለቲካ ሴራ የከለከሏትና ለዘመናት ለኢኮኖሚ ጥገኝነትና ለታሪካዊ እዳ ሰለባ ያደረጓት አካላት ዛሬም አልቦዘኑም ።
ትናንት በዲፕሎማሲና በፖለቲካዊ መጋረጃ ተደራጅተው ሀገሪቱን መተንፈሻ ያሳጡና ወደ መሬት ዝግነት የገፏት ኃይሎች፣ ዛሬም በተመሳሳይ መልኩ በጋራ ተደራጅተው ኢትዮጵያን ከባህር በር አጀንዳዋ ለማራቅ እና በውስጥ ግጭቶች ውስጥ ብቻ እንድትማስን ለማድረግ የሴራ ፖለቲካ ጉንጉናቸውን ሌት ተቀን እየፈተሉ ይገኛሉ።
የህዝቡን ፅኑ አንድነት ለመበጣጠስ፣ በሰው ሰራሽ ልዩነቶችና በአካባቢ ፖለቲካ ውዝግቦች ውስጥ እንድንጠመድ በማድረግ፣ ትልቁን የባህር በር ራዕያችንን እንድንረሳ ለማድረግ የሚጥሩትም ለዚሁ ስውር ዓላማቸው ስኬት ነው።
ነገር ግን የዛሬዋ ኢትዮጵያ ትናንት የነበረችው መብቷን ተነጥቃ የምታለቅስ ምስኪን አገር አይደለችም። የሴራው መጋረጃ ሙሉ በሙሉ ተቀዷል።
ወጣቱ በትምህርቱና በሀገራዊ ስሜቱ፣ ምሁሩ በዕውቀቱና በስትራቴጂካዊ ጥናቱ፣ ህዝቡም በጽኑ ብሔራዊ አንድነቱና በንቃተ ህሊናው ከፍ ብሎ ነቅቷል።
ኢትዮጵያ በየትኛውም ዓይነት ውጫዊ ጫና፣ ውስጣዊ ውዥንብርና መሰናክሎች ውስጥ አልፋ፣ አሁን ላይ ለዘመናት ለቁጭትና ለሐዘን ለኖረው የባህር በር ጥያቄዋ አስተማማኝ፣ ዘላቂና ህጋዊ ምላሽ ማግኘት የምትችልበትን አዲስ ስልታዊና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ በቁርጠኝነት ቀይሳለች።
ይህንን የጀመርነውን የሉዓላዊነትና የክብር መንገድ ደግሞ የፈለገ ዓይነት ማዕበልና ጋሬጣ ቢመጣ ፈጽሞ አንለቀውም።
ስለሆነም፣ በሚፈበረኩ ጊዜያዊ አጀንዳዎች የምንሰናከልበት፣ በውስጥ ውዝግቦች የምንዘናጋበትና ትኩረታችን የሚበታተንበት ዘመን ለዘለዓለሙ አብቅቷል።
የኢትዮጵያ ህዝብ እጁን ለታላቅ ልማት፣ ልቡን ለአስተማማኝ አንድነት፣ ዓይኑን ደግሞ ወደ ታሪካዊውና ተፈጥሯዊው የባህር ደጃፉ አድርጓል። ምንም ዓይነት በተቀናጀ መንገድ የተደራጀ የውስጥና የውጭ ሴራ ይህንን ብሔራዊ ንቅናቄ ሊያስቆመው ወይም ትኩረቱን ሊያስቀይረው አይችልም።
ጉዟችን ወደ ባህር በር ነው፤ ክብራችንን የምንመልስበት፣ ቀጠናዊ ሚናችንን የምናጸናበትና ለቀጣዩ ትውልድ የበለፀገች ኩሩ ሀገር የምናስረክብበት ታላቁ ብሔራዊ አጀንዳችን ሬም፣ ነገም፣ እስከወዲያኛውም የባህር በራችን ነው!
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ