(የዕለቱ መልዕክት)
ማዕበል በሚበዛበት የለውጥ ባሕር ላይ የምትጓዝ ሀገር መዳረሻዋ የሚወሰነው በማዕበሉ ጥንካሬ ሳይሆን በቅንጅቱ ጥበብ እና በመሪው ጽናት ነው።
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ያሳለፈችው የሪፎርም ጉዞ ከተለመደው የዕርዳታ ትርክት ወጥታ፣ በገዛ እጆቿ እና አዕምሮዋ አዲስ ታሪክ መጻፍ እንደምትችል ያረጋገጠችበት የታሪክ እጥፋት ነው።
ይህ ሽግግር ከፖለቲካዊ ስብራት እና ከኢኮኖሚያዊ ድቀት የመነጨውን አሮጌ አጥር ሰብሮ፣ በ"መደመር" እሳቤ ላይ የቆመ አዲስ ሀገራዊ መሠረት ጥሏል።
የሪፎርሙ ስልታዊ አስኳል "መፍጠር፣ መፍጠን እና መዝለል" በሚሉ መርሆች ላይ የተቃኘ ሲሆን መንግሥት፣ ገበያ እና ማኅበረሰብ በተቀናጀ ኃላፊነት የሀገር ግንባታን በጋራ እንዲመሩ አድርጓል።
የዚህ ለውጥ ዋነኛ ማሳያ የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያው ያስመዘገበው እመርታ ነው። ቀደም ሲል የነበረውን የበጀት ዲሲፕሊን መላላት እና ከፍተኛ የውጭ ዕዳ ሥርዓት በመቀየር፣ ብሔራዊ ባንክ ለመንግሥት የሚሰጠውን ቀጥተኛ ብድር ሙሉ በሙሉ በማቆም መረጋጋትን ፈጥሯል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የነበረበትን ግዙፍ ዕዳ ወደ ቦንድ በመቀየር እና ካፒታሉን በሦስት እጥፍ በማሳደግ የፋይናንስ ዘርፉን ከቀውስ መታደግ ተችሏል። ይህ የፖሊሲ ለውጥ የወጪ ንግድ ገቢን ወደ 8.33 ቢሊዮን ዶላር ማሳደጉ የሪፎርሙን ተጨባጭ ፍሬ ያሳያል።
እንዲሁም ግብርናን ማዘመን እና ከኢንዱስትሪ ጋር ማስተሣሠር የሽግግሩ ሌላኛው ምሰሶ ሆኗል። በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 1.3 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ማልማት መቻሉ እና ሩዝን እንደ ስትራቴጂያዊ የሚሊኒየም ሰብል መለየቱ የምግብ ሉዓላዊነትን በተግባር ያረጋገጠ ነው።
“ኢትዮጵያ ታምርት” በሚለው ብሔራዊ ንቅናቄም የአምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ከ47 ወደ 67 በመቶ አድጓል፤ 96 ምርቶችንም በሀገር ውስጥ ለመተካት የተያዘው ስትራቴጂ የውጭ ምንዛሬን መታደግ አስችሏል።
የዲጂታል ትራንስፎርሜሽኑም ስኬት ኢትዮጵያን ከቴክኖሎጂ ጥገኝነት ወደ ቴክኖሎጂ አመንጪነት እያሸጋገራት ይገኛል። የ"ፋይዳ" ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ከ41 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን በማካተት ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር መተሳሰሩ ዘመናዊ አሠራርን አንግሧል።
ከ5 ሚሊዮን በላይ ወጣቶችን በዌብ ፕሮግራሚንግ እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት ያሰለጠነው የ"5 ሚሊዮን ኮደሮች" ኢኒሼቲቭ ደግሞ ወጣቱን ለዓለም አቀፍ ገበያ እያዘጋጀው ነው።
ይህ ሁለንተናዊ የሪፎርም ጉዞ፣ በሀገር ውስጥ የተገነቡ ግዙፍ የመሠረተ ልማት ኮሪደሮች፣ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የታዳሽ ኃይል እመርታ፣ የገለልተኛ ተቋማት ግንባታ እና የብሔራዊ ምክክር ጅምሮች ተዳምረው የኢትዮጵያን ብሩህ ተስፋ ያበስራሉ።
ዛሬ ኢትዮጵያ በችግሮቿ ሳይሆን በእምቅ አቅሟ እና በተግባራዊ ስኬቷ የምትገለጽበት አዲስ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች፤ ይህ ጉዞ ደግሞ ለትውልድ የሚሻገር የጽናት መሠረት ነው።
የኢቢሲ ዶትስትሪም ኤዲቶሪያል