የሰው ልጅ ታሪክ የፈተና እና የመሻገር ትርክት ነው። ሀገር ሲፈርስ፣ ወንድም በወንድሙ ላይ መሣሪያ ሲያነሳ፣ እና የጥፋት ደመና ሲያጠላ መፍትሔው አንድ እና አንድ ብቻ ነው።
ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ መምጣትና መመካከር፤ ይህ እውነት የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ ዓለም አቀፋዊ የሥልጣኔ ሕግ ነው።
ዛሬ በስልጣኔ ማማ ላይ የተቀመጡ በርካታ የዓለም ሀገራት፣ በከፋ የጥፋት እና የእርስ በእርስ መጠላለፍ አዘቅት ወጥተው ቆም ብለው አስበው በመመካከር በመግባባት ልዩነቶችን በማረቅ የተሻገሩ ናቸው።
ልዩነት አይኑር አይባልም፣ ተፈጥሯዊ ስለሆነ ፣ልዩነት ሀገር ላይ ጉዳት ሳያደርስ የሚስተናገድበትን ሥርዓት ተመካክሮ ማበጀት ደግሞ የስልጣኔ ምልክት ነው።
በተለያዩ ዘመናት ይህን እውነታ የገባቸው ትውልዶች መራራውን የግጭትና የጦርነት ገፈት ከቀመሱ በኋላ፣ መፍትሔው በጠመንጃ አፈሙዝ ሳይሆን በሀሳብ ጠረጴዛ ላይ መሆኑን ተረድተው ሀገራቸውን ታድገዋል።
ታሪክ ሁልጊዜም ቢሆን ይህን መንገድ ለሚመርጡ ቁርጠኛ ልጆች ዕድል ትሰጣለች። የኢትዮጵያ ያለፉት ዘመናት የፖለቲካ ጉዞ ውይይትን በመጸየፍ፣ የተለየ ሀሳብን በማጥፋት እና "የኔ ሀሳብ ካልሆነ ሀገር ይፍረስ" በሚል እብሪት የተሞላ ነበር።
የስልጣን ምንጭ ከጠመንጃ አፈሙዝ ብቻ ሲፈለግ የኖረበት ያ የጥፋት መንገድ፣ ሀገራችንን በሁለት ጽንፍ በያዙ ነጠላ ትርክቶች እንድትታመስና የጋራ ሀገራዊ ራዕይ እንዳይኖረን አድርጎ ውድ ዋጋ አስከፍሎናል።
ዛሬ ግን ይህ ትውልድ ቆም ብሎ ራሱን በሐቅ ጠይቋል "ምን ቀረን ካለመመካከር ውጪ?" የሚለው ጥያቄ የትውልዱ ሆኗል፡፡
በሀሳብ ልዩነት ሰበብ ዜጎች ከሀገር ሲሰደዱ፣ አይተናል። ስንት ታሪክ የሚቀይሩ ብሩህ ወጣቶች በከንቱ ሜዳ ላይ ወድቀው ሲቀሩ ተመልክተናል፡፡ አንድ ትውልድ ሲረግፍ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። አሁን ላይ ይህ ትውልድ የትላንት ቁስሎችን እያየና እያስተዋለ ነው። ደግሞ ለመታኮስና የደም ዘመንን ለመቀጠል ፍላጎት የለውም።
አውሮፓውያን በምክንያታዊነት ዘመን የጡንቻና የጉልበት የታሪክ ምዕራፎቻቸውን ወደ ምርምር ውይይትና ምክክር እንዲዞር የወሰኑበት ነው። ሩዋንዳ በደቡብ አፍሪካ፣ ሰሜን አየርላንድ ኮሎምቢያ የመሳሰሉ ሀገራት የሆነ ወቅት በቃ ብለው የቆረጡ ትውልዶች በነቃ ወሳኔ ለዘላቂ ሰላም የወሰኑባቸው ሀገራት ናቸው።
አሁን ላይ ይህ ትውልድ ወደ ሀሳብ ጠረጴዛው ለመምጣትና የሰላምን መንገድ ለመከተል የሚከተሉትን ፅኑ ውሳኔዎች መወሰን አለበት፡-
👉የሀሳብ ልዕልናን ማክበር፡- የጠመንጃን አምባገነንነት በምክንያት፣ በዕውቀት እና በሰላማዊ ውይይት አቅም መተካት።
👉ብሔራዊ መግባባትን ማብሰር፡- በመነጋገር ውስጥ የሃሳብ ልዩነቶችን በማጥበብ የተሰበረውን ሀገረ መንግሥት በጋራ ጠረጴዛ ዙሪያ መጠገን።
👉በጋራ ሀገር ለመገንባት መነሳት፡- የፀና ሀገር ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ልዩነቶችን አርቆ ለብሔራዊ ጥቅም በጋራ በሚቆሙ ትውልዶች ነው የሚገነባው ስለሆነም ይህ ትውልድ ቁርጠኛ ውሳኔ ማሳለፍ አለበት።
ብሔራዊ ምክክር ለእኛ የቅንጦት ወይም የውጭ ኃይላትን ማስደሰቻ ጉዳይ ሳይሆን፣ ቃል በቃል የህልውናችን እና የመቀጠላችን መሠረት ነው። በመሆኑም፣ ዛሬ የተከፈተውን የመመካከር በር ወለል አድርጎ በመጠቀም፣ ኢትዮጵያን በጽኑና በማይናወጥ መሠረት ላይ ለመገንባት በጋራ እንነሳ።
ይህ ትውልድ ታሪካዊ ስህተቶችን አይደግምም፤ ካለመመካከር ጀርባ ጥፋት እንጂ መፍትሔ እንደሌለ ያውቃል። ከመመካከር በስተጀርባ ግን ታላቅና የጸናች ሀገር አለችና ትውልዱ ተመካክሮ፣ ተደምጦ፣ ተከባብሮ በድል ይሻገራል።
በአዶኒያስ ወ/አረጋይ