Search

የጸና ሰላምና የቀና ሥርዓት፦ የኢትዮጵያ የስምንት ዓመታት ያልተቋረጠ ጥረት

ሓሙስ ሚያዝያ 22, 2018 17

ኢትዮጵያ ካለችበት መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና ውስብስብ የታሪክ ሂደት አኳያ፣ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ የህልውናዋ መሠረት ነው። ሀገራችን ለዘመናት ከከፋፋይ ትርክቶች፣ ከውስጥ ፖለቲካዊ መዋቅር ድክመቶችና ከጂኦፖለቲካዊ ሽኩቻዎች የሚመነጩ የሰላም ፈተናዎችን ስታስተናግድ ቆይታለች። በተለይም የታሪክ ትርክቶች ወጥ የሆነ ሀገራዊ መግባባት ከመፍጠር ይልቅ፣ አንዱን ወገን ባለቤት ሌላውን ደግሞ ባዕድ የሚያደርጉ ጽንፈኛ አመለካከቶች እንዲነግሱ በማድረጋቸው፣ ለውስጣዊ ግጭቶች መባባስ እንደ ማገዶ ሆኖ ማገልገሉ ይታወቃል።

የፖለቲካ ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ ከመፈታት ይልቅ ወደ ኃይል አማራጭ እንዲያመሩ ያደረገው ጠንካራና ገለልተኛ የሆኑ ተቋማት አለመኖራቸው ሲሆን፣ ይህም የሰላም እጦቱን ሥር የሰደደ ችግር አድርጎታል። ከዚህ በተጨማሪ የቀይ ባሕር አቅራቢያ መሆኗና የአባይ ወንዝ ምንጭነቷ፣ ታሪካዊ ጠላቶች በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዲገቡና በሀገር ውስጥ ባሉ "ባንዳዎች" አማካኝነት የጥፋት አጀንዳቸውን እንዲያስፈጽሙ በር ከፍቷል።

ይሁን እንጂ ባለፉት ስምንት የለውጥ ዓመታት የለውጡ መንግሥት ይህንን የታሪክ አዙሪት ለመስበርና በሰላማዊ መንገድ የሚደረግ የፖለቲካ ውድድርን ለማስፈን በሆደ ሰፊነት ረጅም ርቀት ተጉዟል። ሰላም ማለት የጥይት ድምፅ አለመስማት ብቻ ሳይሆን ዜጎች ያለሥጋት የሚኖሩበት፣ ልማት የሚፋጠንበትና ጠንካራ ሀገረ-መንግሥት የሚገነባበት መሆኑን በመገንዘብ፣ የመደመር መንግሥት የጸና ሰላምንና የቀና ሥርዓትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሠራ ይገኛል። የመንግሥት የሰላም እሳቤ አዎንታዊ ሰላምን ማረጋገጥ ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ ይህም ግጭት የሌለበትን ሁኔታ ብቻ ሳይሆን ለግጭት መንስኤ የሆኑ መዋቅራዊ ችግሮች እንደ ድህነት፣ ኢ-ፍትሐዊነትና መገለል የተቀረፉበትን ሁኔታ መፍጠር ነው። ይህ ጥረትም ከቀጠናዊ ሰላም ትስስርና "የአፍሪካ ችግር በአፍሪካውያን መፍትሔ" ከሚለው መርህ ጋር ተሳስሮ እየተከናወነ ይገኛል።

የለውጡ መንግሥት ወደ ሥልጣን እንደመጣ በሐሳብ ልዩነት ተሰደው የነበሩ የፖለቲካ ኃይሎች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ጥሪ በማቅረብ ደማቅ አቀባበል አድርጓል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመራው ይህ የሰላም ጉዞ፣ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የዘለቀውን የኢትዮ-ኤርትራ የጠላትነት ግንኙነት ወደ ወዳጅነት የቀየረና በጎረቤት ሀገር ደቡብ ሱዳንም የሰላም ጥረት እንዲሳካ ያደረገ በመሆኑ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዓለም የሰላም ኖቤል ሽልማት እንዲሸለሙ አስችሏል። ሰላም ተኮር ሥራዎችን ተቋማዊ ለማድረግም የሰላም ሚኒስቴር ተቋቁሞ ችግሮችን በንግግር የመፍታት ባሕል እንዲዳብር እየተሠራ ሲሆን፣ የፀጥታና ደኅንነት ተቋማትም ከፖለቲካ ወገንተኝነት የጸዱ እንዲሆኑ ሪፎርም ተደርገዋል።

በሀገራችን ተከስቶ የነበረውን የሰሜኑን ጦርነት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በሰላማዊ መንገድ መቋጨት መቻሉ፣ የጦር ሜዳ ድልን ወደ ዘላቂ ሰላም የመለሰ ታላቅ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ሆኖ ተመዝግቧል። ይህም በትግራይ፣ በአፋርና በአማራ ክልሎች የነበረው ጦርነት ቆሞ ዜጎች ወደ መደበኛ ሕይወታቸውና ልማታቸው እንዲመለሱ አድርጓል። ከዚህ በተጨማሪ የዘመናት ቅራኔዎችን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ሥራ የገባ ሲሆን፣ በትጥቅ ትግል ውስጥ የነበሩ ኃይሎችን ወደ ሰላማዊ ሕይወት ለመመለስም የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን እየሠራ ይገኛል።

እነዚህ ሁሉ ሥራዎች የኢኮኖሚ መረጋጋትን ከመፍጠር ባለፈ፣ ኢትዮጵያ በቀጠናው ሰላምን የምታስከብርና ተሰሚነት ያላት ሀገር ሆና እንድትቀጥል አድርገዋል። የግጭት አዙሪቱን ሰብሮ ወደ ብልጽግና ለመሻገር የዕርቅና የሰላም መንገድ ምትክ የሌለው መሆኑን በማመን መንግሥት እየሠራ ሲሆን፣ በቀጣይም ሰላምን የሚያደፈርሱ አካላትን በሕግ ከመግታት ባለፈ፣ አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታትና የሚያሻግር ገዢ ትርክት የመገንባት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል። በመሆኑም ዘላቂ ሰላም የሚረጋገጠው በጠመንጃ አፈሙዝ ሳይሆን በሐሳብ የበላይነት መሆኑን በመገንዘብ፣ ልዩነቶችን ወደ ጸጋ በመለወጥና የጋራ ብሔራዊ ማንነትን በማጠናከር ለትውልድ የምትበቃ የበለጸገች ኢትዮጵያን የመገንባቱ ሂደት የማይቀለበስ ታሪካዊ ግዴታ ይሆናል።

በረከት ሽመልስ