በማይክሮ-ኢንጂነሪንግ ዘርፍ ትልቅ ስኬት ያስመዘገበው በህንድ ማሃራሽትራ ግዛት ናግፑር ከተማ የሚኖረው የ17 ዓመቱ ሂተን ዳርፑሬ፣ የአለምን ትንሹን የሮቦት እጅ (ሮቦቲክ ክንድ) በመስራት አዲስ የድንቃ ድንቅ መዝገብ የአለም ሪኮርድ አስመዝግቧል።
ይህ ስኬት ይፋ የሆነው የፈጠራ መሳሪያው ልኬት ከተረጋገጠ በኋላ ሲሆን፣ ርዝመቱም 39.25 ሚሊሜትር (1.54 ኢንች) ብቻ ነው።
ሂተን በአውሮፓውያኑ 2024 በ44.49 ሚሊ ሜትር መጠን በኬልተን ሴራ የተያዘውን የአሜሪካን ሪኮርድ በ5 ሚሊ ሜትር ማሻሻል ችሏል።
በማይክሮ-ሮቦቲክስ ዘርፍ ከፍተኛ ፍላጎት ያለው ይህ ወጣት ፈጣሪ የወደፊት አላማውን ሲገልፅም በየዓመቱ አዳዲስ አለም አቀፍ የፈጠራ ሪኮርዶችን በመስበር ራሴን የመፈተን ግልፅ አላማ አለኝ ሲል ተናግሯል።
ሂተን በዚህ ስኬቱ ሳይወሰን በላቀ የቴክኖሎጂ ዘርፍ ተጨማሪ የአለም ሪኮርዶችን ለሀገሩ ህንድ ለማስመዝገብ አልሞ እየሰራ ይገኛል።
በሲሳይ መንግስቱ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: