በኢትዮጵያ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ጉዞ ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪውን ዋነኛ ምሰሶ ለማድረግ ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል።
የዚህ ስትራቴጂ ማጠንጠኛ የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት እና የተፈጥሮ ሀብቶችን እሴት በመጨመር ለፋብሪካዎች በግብዓትነት ማቅረብ ነው።
ኢትዮጵያ አጠቃላይ የመስታወት ፍላጎቷን በውጭ አምራቾች ላይ ጥገኛ ሆና ስታሟላ በመቆየቷ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ስታወጣ ኖራለች።
ለዚህ ማሳያ በፈረንጆቹ 2023 ብቻ ለመስታወት እና የመስታወት ውጤቶች 69.2 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጪ መደረጉ ነው።
ይህን መሠረታዊ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት፣ ጥሬ ዕቃውን በሀገር ውስጥ ከሚገኝ የሲሊካ አሸዋ እና የማዕድን ኦር አቅልጦ ወደ ምርት የሚቀይር፣ በዓመት 600 ሺህ ቶን የማምረት አቅም ያለው ግዙፍ የመስታወት ፋብሪካ በአዲስ አበባ አቃቂ አካባቢ በመገንባት ላይ ይገኛል።
ይህ የኢንዱስትሪ እርምጃ መንግሥት ከነደፋቸው የረጅም ጊዜ የመሠረተ ልማት እና የቤት ግንባታ ፕሮግራሞች ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው።
በሚቀጥሉት 5 ዓመታት 1.5 ሚሊዮን ቤቶችን ለመገንባት ለተያዘው ሀገራዊ ዕቅድ መስታወት፣ ሲሚንቶ እና ብረት ቀዳሚ ግብዓቶች ናቸው።
ለአንድ ቤት ግንባታ በአማካይ ሁለት ሚሊዮን ብር ቢሰላ፣ ጠቅላላ ፕሮጀክቱ ከ3 ትሪሊዮን ብር በላይ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ እና የአጠቃላይ ሀገራዊ ምርትን (GDP) 20 በመቶ ገደማ የሚሸፍን ነው።
በመሆኑም መስታወትን በሀገር ውስጥ በማምረት የኮንስትራክሽን ወጪን መቀነስ የዜጎችን የኑሮ ውድነት ጫና ለማቃለል እንዲሁም በአጭር ጊዜ ለሚገጣጠሙ ዘመናዊ መኖሪያ ሕንፃዎች ምርቱን በበቂ መጠን ለማቅረብ እጅግ ወሳኝ ነው።
ከኮንስትራክሽን ዘርፉ ባለፈ በምግብ፣ መጠጥ እና መድኃኒት አምራች ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ምክንያት የመስታወት ውጤቶች ፍላጎት በከፍተኛ መጠን እያደገ መጥቷል።
ቀደም ሲል በነበረ መረጃ በዓመት ከሚፈለገው 265 ሚሊዮን የማሸጊያ መስታወት ውስጥ የሀገር ውስጥ አምራቾች የሚሸፍኑት አንድ አራተኛውን ብቻ ነበር።
ይህን ክፍተት ለመሙላት በደብረ ብርሃን የሚገኘው ጁኒፐር የመስታወት ፋብሪካ 78 በመቶ ጥሬ ዕቃውን ከአካባቢው የሲሊካ አሸዋ በመጠቀም በዓመት 200 ሚሊዮን ጠርሙሶችን እያመረተ ይገኛል።
በተመሳሳይ በደብረ ብርሃን የሚገኘው ዴዳ የመስታወት ፋብሪካ 86 በመቶ ግብዓቱን ከለሚ አካባቢ የኖራ ማዕድን በመውሰድ በቀን 450 ሺህ ጠርሙሶችን የማምረት አቅም ፈጥሯል።
የዴይላይት አፕላይድ ቴክኖሎጂስ በዓመት 12 ሚሊዮን ጠርሙሶችን እንዲሁም አንጋፋው የአዲስ አበባ ጠርሙስ እና ብርጭቆ ፋብሪካ የማስፋፊያ ሥራውን በማጠናቀቅ በዓመት 250 ሚሊዮን ጠርሙሶችን በማምረት የዘርፉን አቅም አጎልብተዋል።
የእነዚህ አዳዲስ እና የማስፋፊያ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ፋይዳ ፋይዳ ከምርት አቅርቦት ያለፈ እጅግ ትልቅ ነው።
"ኢትዮጵያ ታምርት" በተሰኘው ሀገራዊ ንቅናቄ ማዕቀፍ ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ የገቢ ምርትን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት 5 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ማዳን የተቻለ ሲሆን፣ የመስታወት ኢንዱስትሪው ለዚህ ስኬት የራሱን አዎንታዊ ሚና ተጫውቷል።
በንቅናቄው የተመዘገበው ውጤት እንዳሳየው የአምራች ኢንዱስትሪው የዕድገት ምጣኔ ከ4.8 በመቶ ወደ 13 በመቶ አድጓል።
የፋብሪካዎች የማምረት አቅም አጠቃቀም ወደ 65 በመቶ ከፍ ማለቱ እና የኢንዱስትሪው የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት በ40 በመቶ መጨመሩም የተጀመረው መዋቅራዊ ሽግግር በትክክለኛ መንገድ ላይ መሆኑን ያረጋግጣል።
የመስታወት ኢንዱስትሪው ከማዕድን ማውጣት እስከ ግንባታ ያለውን የእሴት ሰንሰለት በማስተሳሰር ከገቢ ጥገኝነት ራስን ወደ መቻል ለሚደረገው ጉዞ ደማቅ ዐሻራ እያኖረ ይገኛል።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: