Search

የኢትዮ ጂቡቲ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በተደረገው የሪፎርም ሥራ ዛሬ ላይ 43 ቢሊየን ብር ትርፍ እያስገኘ ነው፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ሓሙስ ኅዳር 17, 2019 97

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት 7ኛው የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ እየተካሄደ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፣ የኢትዮ ጂቡቲ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ከጥቂት ዓመታት በፊት 3.4 ቢሊየን ገደማ ትርፍ ያመጣ እንደነበረ አስታውሰው፣ በተደረገው የሪፎርም ሥራ ዛሬ 43 ቢሊየን ብር ትርፍ ያስገኛል ብለዋል።

ኮርፖሬሽኑ የኤሌክትሪክም የነዳጅም ተደምሮ 11 ገደማ የባቡር ፉርጎዎች እንደነበሩ እና ዛሬ ወደ 36 የሚጠጉ የባቡር ፉርጎዎች መታጠቅ መቻሉን ገልጸዋል። ጋሪዎቹም 560 ገደማ እንደነበሩና አሁን ከ1 ሺህ በላይ መድረሳቸውን ጠቁመዋል።

በዚህም በትራንስፖርትና በካርጎም ከፍተኛ የሆነ እመርታ ማምጣቱን ገልጸው፣ በመንገደኞች ከጥቂት ዓመታት በፊት 198 ሺህ መንገደኛ በዓመት ያስተናግድ የነበረው የባቡር ኮርፖሬሽን፣ ዛሬ 578 ሺህ ሰው ማስተናገድ መቻሉን አብራርተዋል።

ከካርጎ አንጻር ከ1.3 ሚሊየን ቶን ካርጎ ወደ 4.2 ሚሊየን ቶን ካርጎ አድጓል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በማብራሪያቸው።

ከ95 በመቶ ያላነሰ ቡና ኤክስፖርት የምናደርገው በባቡር ይፈጸማል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ 25 በመቶ ገደማ የሚጠጋ የማዳበሪያ ኢምፖርት በባቡር እንደሚመጣ ጠቁመዋል።

በሰበታ አካባቢ የባቡር መጫኛ ማውረጃ ፖርትን ጨምሮ ከ15 ኪሎ ሜትር ያላነሰ የባቡር መንገድ ሙሉ በሙሉ በራስ አቅም መገንባት መቻሉንም ጠቅሰዋል።

በተለያየ አካባቢ መሰል ሥራዎች ከሠራን በኋላ ሁለት የባቡር ኩባንያዎቻችን አንደኛው ከአዋሽ እስከ ኮምቦልቻ፣ ሁለተኛው ከኮምቦልቻ እስከ ሀራ ገበያ ያለውን በውስጥ አቅም ቀሪ ሥራዎች ለመሥራት በባለፈው ዓመት አጋማሽ ገደማ ጀምረን በጣም ሰፊ የሚባል እመርታ ታይቷል ብለዋል።

በአድማሱ አራጋው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: