ኢትዮጵያ በ“ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት ከ6 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ወጪ ማስቀረት መቻሏን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የገለጹት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ፣ በንቅናቄው አማካኝነት በኢንዱስትሪው ዘርፍ በተከናወኑ ዘርፈ-ብዙ ተግባራት የሀገር ውስጥ የማምረት አቅም በከፍተኛ ደረጃ ማደጉን ጠቁመዋል።
በዚህም የተገኘው ውጤት አበረታች መሆኑን በመግለጽ፣ የኢንዱስትሪውን ምርትና ምርታማነት ይበልጥ ማስፋትና ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በተለይም በድንጋይ ከሰል፣ በብረታ ብረት፣ በሴራሚክስና በመስታወት ምርቶች ላይ በትኩረት በመሠራቱ ከፍተኛ ለውጥ መመዝገቡ ተገልጿል።
ቀደም ሲል ከ6.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ በማውጣት ከውጭ ይገቡ ከነበሩ ምርቶች መካከል፣ ከ6 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚሆነውን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት መቻሉን ጠቅሰው፣ ይህም እንደ ሀገር ትልቅ እመርታ መሆኑን ገልጸዋል።
የንቅናቄው ዋነኛ ዓላማም ኢትዮጵያ የሚያስፈልጓትን መሠረታዊ ምርቶች በራስ አቅም ማምረት መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያን የሲሚንቶ ፍላጎት በበቂ ሁኔታ ለማሟላት ሰፋፊ የልማትና የማስፋፊያ ሥራዎች መሠራታቸው እንዲሁም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸው ተገልጿል።
በመሐመድ ፊጣሞ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: